(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 26/2010) በዚምባቡዌ ከተካሄደው ምርጫ ጋር በተያየዘ በዋና ከተማዋ ሀራሬ በተከሰተ ግጭት ሶስት ሰዎች ተገደሉ።
በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ገዥው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ አጭበርብሯል የሚሉ በርካታ ወጣቶች በጎዳናዎች ላይ ድንጋይ በመርወርወር ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በዚህ ወቅት ወታደሮች ድንጋይ ሲወረውሩ በነበሩት ተቃዋሚዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ የሶስት ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ተነግሯል።
ኤም ዲ ሲ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ ስብስብ መንግስት የወሰደውን ርምጃ ያልተመጣጠነ እና ፍትሃዊነት የጎደለው በማለት ገልፆታል።
ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ማናጋጓዋ በበኩላቸው የኤም ዲ ሲ የተቃዋሚ ፓርቲ ስብስብ መሪዎች ግጭቱን ይደግፋሉ በማለት ወቀሳ አቅርበዋል።
እናም ደጋፊዎቻቸው ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የፓርቲው አመራሮች የሀገሪቱን ሰላም በማወክና የምርጫ ሂደቱን በማደናቀፍ ተጠያቂ ናቸው በማለትም ፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎቹን አውግዘዋል።
በዚምባቡዌ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ከ210 የፓርላማ ወንበሮች 145ቱን አሽንፏል ተብሏል።
የተቃዋሚ ፓርታዎች ስብስስብ ኤም ዲ ሲ 60 ፣ ኤን ፒ ኤፍና በግሉ የተወዳደረ ግለሰብ አንድአንድ መቀመጫዎች ማሸነፋቸውም ታውቋል።
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ቀሪዎቹ ሶስት የፓርላማ መቀመጫዎች ይፋ እንዳልተደረጉ ታውቋል።
በዚምባቡዌ ሀገሪቱ ከእንግሊዝ ቀኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች ጀምሮ ለረጅም አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በግፊት ከመንበራቸው ከለቀቁ በኋላ ምክትላቸው በነበሩት ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማናጋጓዋ ስትመራ ቆይታለች።
የአሁኑንም ምርጫ እሳቸው ማሸነፋቸው ተገልጿል።
በዚምባቡዌ ምርጫውን ለመታዘብ በአፍሪካ ሕብረት ተወክለው ሀራሬ ያመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም ጋር መገናኘታቸውም ታውቋል።