በዘጠኝ ወራት ውስጥ የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ አቅርቦ 181 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ዕቅድ ቢያዝም ማግኘት የተቻለው 99 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ተባለ።
(ኢሳት ዜና ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ/ም) ይህም ከተያዘው ዕቅድ የተሳካው ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲት ዩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፍሪደሞ አመልክተዋል።
ዕቅዱን ማሳካት ያልተቻለበት ዋነኛ ምክንያት የቆዳና ሌጦ ጥራት አለመሻሻሉ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
እንዲሁም ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ የነበሩ ፋብሪካዎች ሥራ አለመጀመራቸው፣ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ማምረት መጀመራቸወና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አለመጠቀማቸው በተጨማሪ ምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በተከሰተው ከፍተኛ የኃይል እጥረት ሳቢያ በርካታ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ለማምረት መገደዳቸውና አንዳንዶችም ጨርሶ እስከመዘጋት መድረሳቸው ይታወቃል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ 32 የቆዳ ፋብሪካዎች፣ 23 የጫማ ፋብሪካዎች፣ አራት የቆዳ ጓንት ፋብሪካዎች እና 19 የቆዳ አልባሳትና እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካዎች አሉ፡፡
ነገር ግን ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ያቀረቡት 26 የቆዳ፣ 14 የጫማ እና ሁለት የቆዳ ጓንት አምራቾች ብቻ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም የገበያ ዋጋ ተመን ያለመሸጣቸው ሁኔታ ሌላው ዘርፉ የተጋረጠበት ችግር ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ለዋጋ ልዩነቱም አንድኛው ምክንያት የፋብሪካዎቹ ዋጋ የመደራደር አቅም ውስንነት እንደሆነ መናገራቸውን ከአዲስ ዘመን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።