ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን ዘይሴ በሚባል ቀበሌ፣ ከ4 ቀናት በፊት አንድ ግለሰብ ከመሬት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት፣ የመሬት አስተዳደር ሃላፊውን ጨምሮ ሌሎች 3 የወረዳ ሹሞችን ገድሏል።
ግለሰቡ በ2007 ምርጫ የተቃዋሚ አባሎችን ደግፈሃል በሚል የያዘውን መሬት እንዲለቅ የመሬት አስተዳዳር ሃላፊው በጠየቁት ጊዜ፣ ” ከአባቴ ያገኘሁትን የውርስ መሬት አልለቅም” በማለት መመለሱን ተከትሎ፣ የመሬት አስተዳደር ሃላፊው በግድ እንዲለቅ እንደሚደረግ ዝቶበት ነበር። የእረሻ መሬቱ ላይ ያለው ሰብል በከብት እንዲበላ ማድረጉን የሚገልጹት የአካባቢው ምንጮች፣ በድርጊቱ የተበሳጨው ወጣት መሳሪያ በማምጣት የመሬት አስተዳደር ሹሙን እና ሌሎችንም ሹሞች ገድሎ ተሰውሯል።
ድርጊቱን ተከትሎ ፖሊስ የገዳዮችን ወላጅ አባትና ቤተሰብ እንዲሁም፣ ከገዳይ ጋር ተባብረው ተቃውሞ አስነስተዋል ያላቸውን በርካታ ሰዎች በመያዝ አርባምንጭ እስር ቤት ማስገባቱን የአካባቢው የመረጃ ምንጭ ገልጸዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ሰአት ገዳይ አልተያዘም።
በሌላ ዜና ደግሞ በከምባ ወረዳ በምርጫው ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲን ደግፋችሁዋል የተባሉ ከ30 ያላነሱ ሰዎች በተለያዩ የወረዳው እስር ቤቶች ታስረው ይገኛሉ። ባልታ በሚባለው እስር ቤት 9፣ በሃ እስር ቤት 5፣ በከምባ 3 እንዲሁም በሻቃሮ እስር ቤት 17 ሰዎች ፍትህ አጥተው ለሳምንታት በእስር እየተንገላቱ ነው። አብዛኞቹ እስረኞች የመንግስት ሰራተኞች ሲሆኑ፣ እስር ቤት መግባታቸውን ተከትሎ ደሞዝ እንዳይከፈላቸው በዚህም ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።
ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው የጠየቁት እስረኞች፣ “ተቃዋሚዎች ይክፈሉዋችሁ” የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን ሃላፊዎች ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።