(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 28/2011) የአውሮፓ ህብረት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የልማት ጉባዔ ሊያዘጋጅ ነው።
በሶማሊያ የህብረቱ ጉዳይ ተጠሪ ፉልጀንሺዮ ጋሪዶ ሩዝ እንደገለጹት ከዓለም ባንክና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር የሚዘጋጀው ጉባዔ በመጪው ሀምሌ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረው አዲስ የግንኙነት መስመር ይበልጥ መጠናከር አለበት የሚል አቋም እንዳለው ነው በህብረቱ የሶማሊያ ልዩ ተጠሪ የገለጹት።
በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በሶስቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው የሰላምና የትብብር ግንኙነት በአውሮፓ ህብረት ዘንድ በልዩ ትኩረት የሚከታተለው መሆኑን የተናገሩት ተጠሪው ፉልጂንሺዮ ጋሪዶ ሩዝ ይህ ዓይነቱን መልካም አጋጣሚ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የሰላም ሂደት በማጠናከር ዘላቂ የሆነ ልማት በሚስፋፋበት መንገድ ላይ የሚያተኩር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጉባዔ ለማዘጋጀት ከውሳኔ ላይ ደርሷል ነው ያሉት ተጠሪው ሩዝ።
ከዓለም ባንክና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር የሚካሄደው ጉባዔ መነሻው በቀጠናው የታየው የሰላም ክስተት ሲሆን መዳረሻው በአከባቢዉ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማምጣት ሰላሙ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል።
ይህንን ታላቅ ጉባዔ ለማተናገድ አዲስ አበባ የተመረጠች ሲሆን በመጪው ሀምሌ ወር ላይ እንደሚካሄድም ተገጿል።
ለጉባዔው መታቀድ በተለይ በኢትዮጵያ ኤርትራና ሶማሊያ መካከል የተጀመረው የሰላም ሂደት ዋናውን ሚና ተጫውቷል ያሉት በህብረቱ የሶማሊያ ልዩ ተጠሪ ጋሪዶ ሩዝ በእነዚህ ሶስት ሀገራት የሚታየው ሰላማዊና አዲስ ግንኙነት ለቀጣይ አጠቃላይ ትብብር መንገድ የጠረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሶስቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር አልፈው ኤምባሲዎቻቸውን በመክፈት ለጀመሩት መልካም ጥረት የአውሮፓ ህብረት ከጎናቸው በመሆን ወደላቀ ደረጃ እንዲደርስ የሚቻለውን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሰሞኑን በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በተከበረው የአውሮፓ ቀን ላይ ንግግር ያደረጉት ልዩ ተጠሪው ጋሪዶ ሩዝ በአፍሪካ ቀንድ ለሚታየው ሰላማዊ ግንኙነት ኢትዮጵያና ኤርትራ ለወሰዱት ቁርጠኛ ውሳኔ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።