(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 13/2010) በኢትዮጵያ እርቅና ሰላም ላይ ያተኮረ ጉባዔ መጥራቱን በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ።
በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶሱ ከህዳር 7 ጀምሮ የሚያካሂደው መደበኛ ጉባኤ ዋነኛ የምክክር አጀንዳው እርቅና ሰላም እንደሚሆን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በመግለጽ ኢትዮጵያውያን የዘር የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርጉ ኢትዮጵያን ለማዳን እንዲሰለፉ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል።
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መሆኗን አጽንኦት በመስጠት ያሳስባል።
እንደ ወቅቱ ሁኔታ ሀገሪቱ ያልፈረሰችው ህዝባችን ፈሪሃ እግዚያብሄር ያደረበትና ጨዋ ስለሆነ እንጂ መንግስት ስለሚያስተዳድረው አይደለም ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ መንግስት የሚባል ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል ይላል በመግለጫው።
በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶሱ ኢትዮጵያውያን በዚህ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እያሳዩ ላለው ጨዋነት ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን በስልጣን ላይ እንዳለው መንግስት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እንደሶማሊያ ትሆን ነበር ሲል ገልጿል።
በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ የሚደረገው መፈናቀልና ግድያ በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት አቀናባሪነት መሆኑን ህዝባችን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ ህዝብ እንደ ህዝብ ይህን ባለመፍቀዱ ልናመሰግነውም ይገባል ብሏል።
ህዝባችን ጨዋ ባይሆን ኖሮ እስካሁንም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም ነበር ያለው የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ፣ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ በማድረግ ይቀጥላል።
እስካሁን የተከተላችሁትን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይዛችሁ በመቻቻል ይህን የመከራ ጊዜ እንድታሳልፉት በማለት ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለምሁራንና ለፖለቲካ ሃይሎችም ወቅታዊ ጥሪ ማድረጉ ታውቋል።
የሀገር ሽማግሌዎች የፖለቲካና የታሪክ ምሁራን ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝና ህዝቡ ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለመታደግ አንድ ሆናችሁ መስራት ያለባችሁ ወቅት አሁን ነው ብሏል ቅዱስ ሲኖዶሱ።
ነገ የዘገየ ነው ምናልባትም እድል ላይኖር ይችላል ያለው መግለጫው ዛሬውኑ ኢትዮጵያን ለማዳን እግዚአብሔር እድሉን ስለሰጠ መረባረብ ያስፈልጋል ሲል አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል።
ይህን ታደርጉ ዘንድ እየተራበ በሚገደለው፣ በሚታሰረ፣ በሚሰደደውና በሚሰቃየው ህዝባችን ስም ጥሪ እናደርጋለንም ብሏል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ የዚህን ዓመት መደበኛ ጉባዔውን በቀጣዩ ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ በአሜሪካን ኦሃዮ ግዛት ኮሎምበስ ከተማ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን ዋናው አጀንዳም የኢትዮጵያ የእርቅና ሰላም ጉዳይ እንደሚሆን በመግለጫው ተጠቅሷል።
መንፈሳዊ የይቅርታና የእርቅ ሂደት ካልተከናውነና የማህበረሰቡ መንፈስ በይቅርታ ካልታደሰ የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ብቻውን ሀገሪቱን ወደሚፈለገው የሰላምና የአንድነት ጉዞ ሊያደርሳት አይችልም ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ የህዳሩ ጉባዔ በእርቅና ሰላም ላይ ይመክራል ሲልም አስታውቋል።