በውጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ኢህአዴግ ከስልጣን እንዲወርድ፣ የትግራይ ተወላጆች ህዝባዊ ተቃውሞውን እንዲቀላቀሉ ጠየቁ

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካና የተለያዩ ሃገራት የሆነ የትግራይ ተወላጆች ገዥው የኢህአዴግ መንገስት ከስልጣን እንዲወርድና በሃገሪቱ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም፣ የትግራይ ተወላጆች በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ትግል እንዲቀላቀሉ ጥሪን አቀረቡ።

36 የሚሆኑ የቀድሞ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) አመራሮችንና አባላትን ያካተተ አንድ ቡድን የትግራይ ተወላጆች ያላቸው አስተዋፅዖ እና ሚና እንዲጠናከር ለማድረግ ዘመቻን እያካሄደ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በተለያዩ ሃገራት ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጥሪውን ያቀረበው ይኸው ቡድን የህወሃት ባለስልጣን በስልጣናቸው ለመቆየት የሚያደርጓቸውን መሰሪ ቅስቀሳዎች የትግራይ ተወላጆች እንዲያጋልጡና የሚፈጽሟቸውን ጭፍጨፋዎች እንዲያወግዙ ጥሪውን አቅርቧል።

ተወላጆቹ ሊያደርጉ ከሚገባው አስተዋፅዖ በተጨማሪ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ትግል እንዲቀላቀሉ ሲሉ ቡድኑ በመግለጫው አመልክቷል።

በቅርቡ 16 አባላትን በማሰባሰብ ተመሳሳይ ጥሪን አቅርቦ የነበረው የትግራይ ተወላጆች ቡድን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመቻውን በመቀላቀል ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ቁጥራቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን አክሎ አስታውቋል።

ገዢው የኢህአዴግ መንገስት የሃገሪቱን ወሳኝ የደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ቦታዎችን በበላይነት ተቆጣጥሮ ይገኛል ሲል የገለጸው ይኸው ቡድን ችግሮቹን ለመቅረፍ ህወሃት/ኢህአዴግን ከስልጣን በማስወገድ ዴሞክራሲያው ስርዓትን መገንባት ወሳኝ አማራጭ መሆኑን አክሎ አመልክቷል።

አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ ስዩም መስፍን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መመስረት አላማቸው እንደሆነ በማኒፌስቶ ከገለፁት ጥቂት የህወሃት መስራቾች ውስጥ ይገኛሉ ሲል ያወሳው መግለጫው አመራሮቹ ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪዎች መስለው የመቅረብ የሞራል ብቃት የላቸውም በማለት አስታውቋል።