ኢሳት (ታህሳስ 21 ፥ 2009)
ኢትዮጵያን ስኳር ላኪ ሃገር ያደርጋሉ ተብለው ከውጭ በተገኘ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ግንባታቸው ከሰባት አመት በፊት የተጀመሩ ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተስተጓጉሎ እያለ ብድር የመክፈያ ጊዜያቸው መድረሱ ተገለጸ።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ የሚገኘው መንግስት በበኩሉ በመገንባት ላይ ያሉትን ጨምሮ በስራ ላይ ያሉ የስኳር ፋብሪካዎች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በሽርክና ለመስራው መወሰኑን ይፋ አድርጓል።
መንግስት ከተለያዩ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት በብድር ባገኘው ገንዘብ የወልቃይት፣ የኦሞ፣ ኩራዝ አንድ ሁለትና ሶስት እንዲሁም የጣና በለስ ቁጥር አንድና ሁለት ፕሮጄክቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል።
ይሁንና ሃገሪቱን ከስኳር እጥረት በማላቀቅ ኢትዮጵያ ምርቷን ወደ ውጭ ሃገር በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያደርጋሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ፋብሪካዎች አብዛኞቹ በጅምር ላይ መቅረታቸው ተመልክቷል።
ፋብሪካዎቹ በከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ውስጥ በመግባታቸውና የተጀመሩ ፕሮጄክቶችን ለማስጨርስ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ በማስፈለጉ ምክንያት መንግስት ነባሮቹንና አዳዲስ ግንባታዎች በሽርክና ለማካሄድ መወሰኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፋብሪካዎቹ በአምስት አመት ውስጥ ወደ ምርት ይገባሉ ተብሎ የተጠበቁ ሲሆን፣ ግንባታቸው በ25 በመቶ ላይ የሚገኝ እንዳለም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ፋብሪካዎች ለሰባት አመት ያህል መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ከአበዳሪ ካላት የተገኘ ብድር የመጀመሪያ ክፍያ የመጀመሪያ ጊዜው መቃረቡን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።
የኮንትራት አስተዳደርና የፋይናንስ ችግሮች ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በሃሙስ ዘገባችን ለጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ ተዘጋጅቶ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ምርት ፋብሪካው ባለመጠናቀቁ ምክንያት ምርቱ እንዲቃጠል መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል።
ከፋብሪካው በፊት ለምርት ደርሶ የነበረው የሸንኮራ አገዳ እንዲወገድ የተወሰነው ምርት ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰበት እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ይገልጻሉ።
በሃገሪቱ ያሉ ጅምርና ነባር የስኳር ፋብሪካዎችን ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በሽርክና ለማስተዳደር የቻይንና የአውሮፓ ሃገራት በመደራደር ላይ ሲሆን፣ መንግስት ያጋጠመው የፋይናንስ እጥረት ወደዚህ አማራጭ እንዲገባ ማስገደዱንም ባለሙያዎች አስተድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የጣና በለስ አንድና ሁለት የስኳር ፕሮጄክቶችን ለአንድ የቱርክ ኩባንያ 75 በመቶ ድርሻን ለመስጠት ሲካሄድ የነበረ ድርድር መቋረጡም ታውቋል።
በዲሳ ግሩፕ የተሰኘ ይኸው የቱርክ ኩባንያ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ገንዘብ በመመደብ የፕሮጄክቱን 75 በመቶ ባለቤትነት ለመረከብ ድርድር ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ ከገንዘብ አከፋፈልና ከትርፉ ክፍፍል ጋር ከመንግስት ጋር ሊደርስ አለመቻሉ ተገልጿል።
ይሁንና ሁለቱም ወገኖች ተፈጥሯል በተባለው አለመግባባት ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።