ኢሳት (መጋቢት 30 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ብድር ላይ ተመስርቶ እያካሄደ ያለው የልማት ፕሮጄክቶች የሃገሪቱ ኢኮኖሚን አደጋ ውስጥ መክተቱንና ሊንኮታኮት እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አሳሰቡ።
መንግስት ከቻይና ብቻ ለመሰረተ-ልማቶች ማካሄጃ 17 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መበደሩን ያስታወቁትና በለንደን ዩንቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ገዳ ሃገሪቱ በአሳሳቢ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ውስጥ መሆኗን እንደገለፀ ዘ-ኢስት አፍሪካን መጽሄት ዘግቧል።
ሃገሪቱ ለውጭ ንግድ ከምታቀርበው ምርት ውስጥ ሶስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ብቻ በአመት እንደምታገኝ ያወሱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፣ የገቢ ንግዱ ግን 13 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ መድረሱን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ሲሆን፣ ይኸው አካሄድ ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ጤናማ አለመሆኑንም ዶ/ር አለማየሁ አስረድተዋል።
ከቻይና መንግስት ከፍተኛ ብድርን ተሸክማ የምትገኘው ሃገሪቱ ቻይና በማንኛውም ጊዜ ብድሯን እንደምታቋርጥ ብትገልጽም የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ ነው ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ህዝብ 17 ቢሊዮን ዶላር ብድርን ሰጥታ የምትገኘው ቻይና ባልታሰበ ሰዓት እንደ ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽጡልኝ የሚል ጥያቄ ብታነሳ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አደጋ እንደሚፈጥርም ዶ/ር አለማየሁ ለመጽሄቱ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለተለያዩ ግብዓቶች በዋነኝነት የሚያስፈልጉትን 77 በመቶ ቁሳቁሶች ከውጭ ሃገር የሚያስገባ በመሆኑም ኢኮኖሚ በጤናማ መሰረተ ላይ አለመቀመጡን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል። ከአመታት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በአሜሪካ ላይ ጥገኛ ሆና የቆየችው ደቡብ ኮሪያም በኢኮኖሚያዋ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶ እንደነበር ዶ/ር አለማየሁ በዋቢነት አቅርበዋል።
የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እንደሚንኮታኮት ማረጋገጥ እፈልጋለሁ ሲሉ የተናገሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና የሰለጠኑ ሰዎችን ለማፍራት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት አክለው ገልጸዋል።
የአለም ባንክና ሌሎች የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለመታደግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ሲያሳስቡ መሰንበታቸው ይታወቃል።