መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ውቤ በረሃ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እስከ አፍንጮ በር የሚገኙ ነጋዴዎች፣ ምትክ የንግድ ቦታ ሳይሰጣቸው የንግድ ቤቶቻቸውን በግዳጅ ለማፍረስ እየታሸጉ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ።
የከተማው አስተዳደር ነጋዴዎቹን ከዓመት በፊት ሰብስቦ በአክሲዮን እንዲደራጁና እያንዳንዳቸው 25,000 ብር በማዋጣት በባንክ እንዲያስቀምጡ እንዲሁም በየወሩ ከ2000 ብር በላይ ገቢ እንዲያደርጉ ያቀረበውን ሐሳብ መቀበላቸውንና ተግባራዊ ማድረጋቸውን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ ፣ በንግድ ቦታቸው ላይ ግንባታ ተካሂዶ እያንዳንዳቸው 25 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው ሁሉ ታጥፎ በቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እኩል ሊባል የሚችል ዕድሜ ያስቆጠሩ ንግድ ቤቶች በአንድ ሳምንት ማስጠንቀቂያ ብቻ ለማፍረስ መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ ፣ አስተዳደሩ የገባላቸውን ቃል በማጠፍ ‹‹ተለዋጭ ቦታ የምሰጣችሁ አሁን ያላችሁበትን የንግድ ቦታ አፅድቼ ስጨርስ ነው›› ማለቱ ከሕግ አንፃር የዜጐችን መብት የማያስከብር በመሆኑ አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡
ቤተሰቦቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት የሚመግቡትና ራሳቸውንም እያኖሩ የሚገኙት በያዙት ንግድ ቤት እየነገዱ በሚያገኙት ገቢ መሆኑን የሚናገሩት ነጋዴዎቹ ፣ በሕገወጥ መንገድ በ‹‹አፍራሽ ግብረ ኃይል›› አማካይነት ወደ ጎዳና ተገፍተው ከመጣላቸው በፊት ለሌሎች ነጋዴዎች የተሰጠው ዕድል ለእነሱም መነፈግ ስለሌለበት ተለዋጭ የኮንዶሚኒየም የንግድ ቦታዎች እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለባለሃበቶች እየተባለ በሚሰጡ ቦታዎች ህዝቡ ምሬቱን እያሰማ ነው።