በውስጥም በውጭም ብዙ ችግሮች እያጋጠሙዋቸው እንደሆነ ጠ/ሚኒስትሩ ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 08 ቀን 2011 ዓ/ም ) ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ ከፓርላማ አባላቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ፣ እርሳቸውን በግል እንዲሁም የለውጡ ሂደት እያጋጠመው ያለውን ፈተና ዘርዝረው አቅርበዋል።
ስራቸውን የሚሰሩት ህይወታቸውን አስይዘው እንደሆነ የገለጹት ጠ/ሚኒስትር አብይ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችም ሆኑ በቅርቡ ወታደሮች ወደ ቤተመንግስት የሄዱበት አካሄድ የግል ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ ለመጣል እና ለውጡን ለመቀልበስ የታሰበ እንደነበር ተናግረዋል።
በተለያየ ቦታ ዜጎች ሲፈናቀሉ ለማጽናናት ወደ ስፍራው ለመሄድ ሙከራ ሲደረግም፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የግድያ ሙከራ ለማድረግ የተደረገበት አጋጣሚ እንደነበር ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አደጋ ብለው የጠቀሱት በቅርቡ ወታደሮች ወደ ቤተመንግስት የሄዱበትን አጋጣሚ ሲሆን፣ የወታደሮቹ እንቅስቃሴ በመሪዎቹ ላይ ጉዳት በማድረስ ለውጡን ለመቀልበስ የተቃጣ እንደነበርና አደጋውን በጥበብ ማክሸፍ እንደተቻለ ተናግረዋል።
“የማይነገር፣ የማይዘረዘር ፈተናው ያለው ከውስጥ” ነው ያሉት ዶ/ር አብይ፣ 20 ሚኒስትሮችን እንኳን ለማሾም የነበረው ፈተና ቀላል አይደለም ብለዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ሚዲያው ለለውጡ እያደረገ ያለውን አወንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎችም አብራርተዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ፣ አገሪቱን መለወጥ ቀላል ስራ እንዳልሆነ እና ትዕግስትና ጽናት የሚጠይቅ መሆኑን በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፣ ከሚኒስትር እስከ ቀበሌ ያለው ሁኔታ ገና ያልተለወጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ህዝብ ካልደገፋቸው በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸውም ዶ/ር አብይ አክለው ገልጸዋል።