ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2009)
ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን በአለም ጤና ድርጅት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ፊት ለፊት በመሰባሰብ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የድርጅቱ ተመራጭ እንዳይሆኑ ተቃውሞ አቀረቡ።
ማክሰኞ ረፋድ ላይ በድርጅቱ ጽ/ቤት የተሰባሰቡት ኢትዮጵያውያን ዶ/ር ቴዎድሮስ ከገዢው ከኢህአዴግ መንግስት ጋር በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ያላቸው የቆየ ትስስር ድርጅቱን ለመምራት እንደማያበቃቸው ሲቃወሙ ታይተዋል።
በትናንትናው ዕለት ታዋቂ የጤና ባለሙያዎች ዶ/ር ቴዎድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ሶስት ጊዜ የተከሰቱ የኮሌራ በሽታ ለህዝብ እንዳይታወቅ አድረገዋል ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል።
ተመሳሳይ ቅሬታን በአለም ጤና ድርጅት የዋሽንግተን ዲሲ ቢሮ ፊት ለፊት ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን ለድርጅቱ ዕጩ ሆነው ያቀረቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ ጉዳዩን በአግባቡ እንዲመለከተው ጥያቄ አቅርበዋል። የአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት በቀጣዩ ሳምንት የመጨረሻው ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡ ሶስት ተፎካካሪዎች መካከል አንደኛውን አሸናፊ ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁንና ከአፍሪካ ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበርካታ ኢትዮጵያውያንና በአለም ጤና ባለሙያዎች ዘንድ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ብቸኛው ተወዳዳሪ መሆናቸው ታውቋል።
ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሰኞ ለንባብ ባበቃው እትሙ የአለም ጤና ድርጅት ባለስልጣናት ሳይቀሩ የኢትዮጵያ መንግስት የበሽታ ወረርሽኝ መደበቁ ስጋት እንዳሳደረባቸው በግል መግለጻቸው በዘገባው ተመልክቷል።
የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ታከለ ሰልፈኞቹ በጽሁፉ ያቀረቡትን ጥያቄ ለአለም ጤና ድርጅቱ ተወካዮች ማስረከባቸውን ለዜና ክፍላችን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰልፈኞቹ በተመሳሳይ እለት ለኢትዮጵያ መንግስት የማግባባት ወይም የድለላ ስራን በሚሰሩ አንድ ድርጅት ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን የሰልፉ አስተባባር አክለው አስረድተዋል።
ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ፖሊሲውን ለአሜሪካ ባለስልጣናት ለማስተዋወቅና ድጋፍ ለማግኘት ሲል የሚያወጣው ገንዘብ የህዝብ ገንዘብ በመሆኑ ድርጅቱ አምባገነን ላሉት መንግስት ድጋፍ እንዳይሰጥ ጥያቄን አቅርበዋል።
መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከወራት በፊት ኤስ ጂ አር (SGR-LLC) ከተሰኘው ተቋም ጋር የማግባባት ስራ ለማካሄድ በየወሩ የ150 ሺ ዶላር ክፍያ ለመፈጸም ስምምነት አድርጎ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በዚህ ተቋም በመገኘት ተቃውሞዋቸውን ያቀረቡት ኢትዮጵያውያን መንግስት የአገዛዙ ዕድሜ ለማራዘም ሲል የህዝብ ገንዘብ ማባከኑን ተረድተው ያደረጉት ስምምነት እንዲያጤኑ ጠይቀዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ግርማ ብሩ ከድርጅቱ ተወካይ ጋር በየካቲት ወር ላይ ይህንኑ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፣ የተደረሰው ውል ለአንድ አመት የሚቆይ ሆኖ የሚራዘም መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።