ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2009)
በዋልድባ ገዳም አቅራቢያ በአማራና በትግራይ ሚሊሺያዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ከሁለቱም ወገን ታጣቂዎች ተገደሉ።
ማክሰኞ መጋቢት 26, 2009 አም ለተቀሰቀሰው ግጭት መነሻ የሆነው በዋልድባ ገዳም ለሚከበረው አመታዊ የመድሃኒያለም በዓል የሚጓዙ የአማራ ሚሊሺያዎች ትጥቅ እንዲፈቱ በመጠየቃቸው እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
በታሪካዊው ዋልድባ አበረንታት ገዳም መጋቢት 27 ለሚከበረው አመታዊ የመድሃኒያለም የንግስ በዓል በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ከዋዜማ ቀናት ጀምሮ ወደገዳሙ እንደሚጓዙ የእሳት ምንጮች ገልጸዋል። አሁንም በተመሳሳይ ለንግስ የሚሄዱ የአማራ ክልል ሚሊሺያዎች ትጥቅ እንዲፈቱ በትግራይ ሚሊሺያዎች ሲጠየቁ፣ የተፈጠረው ውዝግብ ወደ ግጭት አምርቷል።
በግጭቱ ከሁለቱም ወገን ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ማክሰኞ መጋቢት 26, 2009 ምሽት ድረስ ግጭቱ ቀጥሏል።
ለንግስ በዓሉ ሲጓዙ የነበሩት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ የተጠየቁት 300 ያህል የአማራ ክልል ሚሊሺያዎች እንደሆኑም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የዋልድባ ገዳም አካባቢ በተለይም የመቃብር ስፍራውን ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ በሚል የተወሰደውን ርምጃ በመቃወም ድምጻቸውን በማሰማታቸው ሲሰደዱ የነበሩት አባ ገብረየሱስ፣ በቅርቡ መታሰራቸው ይታወሳል። ለ5 አመታት ተሰውረው የነበሩት አባት መታሰራቸውን ተከትሎ፣ በተመሳሳይ 39 መነኮሳት ከገዳሙ ተወስደው በመታሰራቸው በአካባቢው ውጥረት ሰፍኖ መቆየቱን መረዳት ተችሏል።