(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 10/2010) ዛሬ በዋለው የዋልድባ መነኮሳት ችሎት ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መገኘታቸው ታወቀ።
አጋርነትን ለማሳየት በተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የዋልድባ አባቶች መደሰታቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
በካቴና እጆቻቸው አንድ ላይ ታስረው የሚታዩበት ፎቶግራፍ በማህበራዊ ሚዲያዎች መሰራጨቱን ተከትሎ ቁጣ መነሳቱም ታውቋል።
በችሎቱ አካባቢ ፎቶግራፍ አንስታችኋል ተብለው የታሰሩ እንዳሉም ተገልጿል።
በአባቶቹ ላይ እየተፈጸመ ያለው ስቃይ እንዲቆም የሚጠይቅ ዘመቻም ሊደረግ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ሁለት ጊዜ ክሳቸው ተቋርጦ እንደሚፈቱ ተገልጾ ነበር።
በሽብርተኝነት ፋይል ተከፍቶባቸው የተፈረደባቸውና ክሳቸው በሂደት ላይ የነበሩ ሲፈቱ እነሱ ግን ክሳቸው እንዲቀጥል ነው የተደረገው።
በማዕከላዊ እስር ቤት በነበሩ ጊዜ በትግራይ ደህንነቶች ተዘቅዝቀው እንዲገረፉ ተደርገዋል።
የክህነት ልባሳቸውን እንዲያወልቁ በሚል በተደጋጋሚ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል።
በጨለማ ቤት ውስጥ ለቀናትና ሳምንታት እንዲቆዩ ተፈርዶባቸዋል።
ለአንድ ዓመት የለበሱትን እንዲቀይሩ ከህዝቡ የተሰጣቸውን ተጨማሪ የክህነት አልባሳት ወደ እስር ቤቱ እንዳይገባ ተከልክለዋል።
የእስር ቤቱን የእስረኞች የደንብ ልብስ እንዲለብሱ በሚል ድብደባና ስቃይ የታከለበት ርምጃ ተወስዶባቸው ለመልበስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መሬት ለመሬት ሲጎተቱ እንደነበርም መዘገቡ የሚታወስ ነው።
አባ ገብረየሱስ ኪዳነማርያምና አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖት የተባሉ የዋልድባ አባቶች ጉዳይ በህዝበ ክርስቲያኑና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ጉዳያቸው ትኩረት እያገኘ ነው።
ዛሬ በዋለው ችሎት ከ200 በላይ ሰዎች መታደማቸው ታውቋል።
በፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ታዳሚዎች እንደገለጹት የዋልድባ አባቶች ባዩት የህዝብ ድጋፍ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በችሎቱ አዳራሽ የነበረው ትዕይንት ስሜትን የሚነካ እንደሆነ በአደራሹ የነበሩ ይናገራሉ።
ቀድሞ የገቡት ታዳሚዎች ሁለቱ የዋልድባ አባቶች እጆቻቸው በካቴና ብረት ታስረው ወደ ችሎቱ አዳራሽ ሲገቡ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው በክብር ሲቀበሏቸው የእስር ቤቱ አጃቢዎች ሃላፊ ኮማንደር እንዲቀመጡ ማስገደዱን የጠቀሱት የዓይን እማኞች ህዝቡ ግን ሁለቱ አባቶች ከወንበራቸው እስኪቀመጡ መጠበቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በችሎቱ አዳራሽ የነበረው ህዝብ የዋልድባ አባቶች በካቴና ታስረው ሲያያቸው ስሜቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ በለቅሶና ኋይታ ለደቂቃዎች መቆየቱን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
አንድ ሰዓት ዘግይተው የተሰየሙት ዳኞች የመነኮሳቱን ጉዳይ በሶስተኛ መዝገብ የተመለከቱ ሲሆን ቅያሪ የክህነት ልብስ እንዲገባላቸው፣ ተለያይተው መታሰራቸው ቀርቶ በአንድ ላይ እንዲሆኑ በቀደመው ችሎት ያስተላለፉት ውሳኔ ተፈጻሚ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ለመጋቢት 18 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን ችሎት አጠናቀዋል።
የዋልድባ መነኮሳት እየደረሰባቸው ያለውን ግፍና ሰቆቃ በተመለከተ በሀገር ቤት የሚገኘው ቤተክህነት ምንም ዓይነት ርምጃ ያልወሰደ መሆኑን ህዝበ ክርስቲያኑን አሳዝኗል።
በዛሬው ችሎት የተገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለመነኮሳቱ ትኩረት በመስጠት በሚቀጥለውም ችሎት ህዝቡ በብዛት እንዲገኝ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የኢሳት ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል።