ኅዳር ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጦርነቱ የተካፈሉ ሰዎች ለኢሳት እንደገለጹት በእንቃሽ በህዝብ በሚደገፉት የነጻነት ሃይሎች በአንድ ወገን የመንግስት ታጣቂዎች በሌላ ወገን ባደረጉት ውጊያ 23 የመከላከያ፣ 4 የጸረ ሽምቅና 3 የአካባቢ ሚሊሺያ ወይም ጉጅሌ ተገድለዋል። 25 የሚሆኑ ወታደሮች የተማረኩ ሲሆን፣ ከ20 በላይ ደግሞ ቆስለዋል። በውጊያው መትረጊስ፣ ክላሽንኮቭ፣ አብራራውና ሌሎችም የቡድንና የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች ከአንድ የመገናኛ ሬዲዮ ጋር ተማርኳል። ለነጻነታቸው በሚታገሉት በኩል ታጋይ ገብሩ ታየና ታጋይ ፈንቴ አየልኝ የተባሉ ታጋዮች መሰዋታቸውን የሚናገሩት ታጋዮች፣ 2 ታጋዮችም ቆስለዋል።
የህወሃት አገዛዝ በ6 ኦራል መኪኖች የተጫኑ ወታደሮችን ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ የነጻነት ሃይሎች በአንድ ወገን የመንግስት ታጣቂዎች በሌላ ወገን ተፋጠው እንደሚገኙ ታውቋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት አገዛዙ በምርኮ የተያዙ ወታደሮችንና የቡድን መሳሪያዎችን እንዲመለሱለት ከሀይማኖት አባቶች እና በአካባቢው ከታወቁ ግለሰቦች አውጣጥቶ ሽማግሌዎችን ልኮ የነበረ ቢሆንም የነፃነት ታጋዮች ሽምግልናውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል ፡፡ ምርኮኞች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እነዚሁ ታጋዮች ገልጸዋል ፡፡ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሚሊሻዎች ተለቀው የተወሰኑት ደግሞ የነፃነት ትግሉን መቀላቀላቸውንም ገልጸዋል።
“ፀረ-ሽምቅ እና የአካባቢ ሚሊሻዎች ለምን ፊት ለፊት እየተላኩ ያለአግባብ እንደሚሰው ሊገባን አልቻለም፣ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ እንጠይቃለን ፣ ወያኔ እኛን እርስ በርስ በማጋደል የእሱን የጭቆና ጊዜ ሊያራዝም አይገባም፣ ከባድመ ጦርነት መማር አለባቸው ፡፡ ከነፃነት ታጋዮች እና ከህብረተሰቡ ጎን ሊቆሙ ይገባል “ ታጋዮቹ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በሌላ ዜና ንብረትነቱ የህወሃት የሆነ ሸዊት ማረቸዲስ የጭነት መኪና ከዲቪዥን ተነስቶ በግጨው በኩል ልዩ ቦታው አየር ማረፊያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ሰሊጥ ጭኖ ሲንቀሳቀስ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጋዮች ደርሰው ሰሊጡ እንዲወርድ ካደረጉ በኃላ መኪናውን ሙሉ በሙሉ አቃጥለውታል ፡፡
በሰላማዊ መንገድ ሲካሄድ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በግድያና እስራት ምክንያት ወደ ሃይል ትግል እየተለወጠ ሲሆን ፣ በተለይ በአማራ ክልል ህዝቡ ራሱን እያደራጀ የነጻነትን ትግሉን በማካሄድ ላይ ነው። አገዛዙ በአስቸኳይ አዋጅ ስም አሁንም አፈናውን አጠንክሮ የቀጠለ ሲሆን በሞጣ የተደረገውን የመምህራን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ተጨማሪ መምህራን መታሰራቸው ታውቋል።
በባህር ዳር ከተማም እንዲሁ ሱቆቻችሁን ያለ አግባብ ዘግታችኋል በሚል ሰበብ ድርጅታቸው ተዘግቶ ለእስር የተዳረጉት ነጋዴዎች ለአራተኛ ሳምንት ፍትህ አጥተው በእስር እየማቀቁ ነው። ከታሰሩት ነጋዴዎች መካከል በጤና እክል ምክንያት የተፈቱ ስድስት ነጋዴዎች ቢኖሩም፣ ቀሪዎቹ 29 ነጋዴዎች ያለማንም ከሳሽ እና ጠያቂ አሁንም በእስር ላይ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በርካታ ወጣቶች አሁንም ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ ሶስት በአራት በሆነች ጠባብ ክፍል ከአርባ በላይ ወጣቶች ተፋፍገው እንደሚያድሩ ማወቅ ተችሏል።
በትላንትናው እለት በባህርዳር ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ በርካታ የጢስ ዓባይ ወጣቶች በጅምላ ታፍሰው ታስረዋል።በባህርዳር ከተማም ምንም የማያውቁ የአስራ አራትና የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊዎች ወደ እስር ቤት እየተወሰዱ ነው።በርካታ እናቶች በምሽት በራቸው እየተሰበረ ልጆቻቸውን እየተነጠቁ ነው። እስረኞችን ወደ ብር ሸለቆ ለመውሰድ መታሰቡን ምንጮቻችን ገልጸዋል።