ኅዳር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ እንቃሽ በሚባለው አካባቢ የሚገኙ የነጻነት ሃይሎች ከህዝብ ጋር በመተባበር በመንግሰት ታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱ በሁዋላ፣ አሁንም ፍጥጫው መቀጠሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
እነዚህ ራሳቸውን ያደራጁ ሃይሎች እንደገለጹት፣ ከትናንት ጀምሮ ቀሳውስቱ በመካከላቸው ትልቅ መስቀል በማቆም ጦርነቱ እንቆም ቢያደርጉም አሁንም ሁሉም ቦታ ቦታውን ይዞ ተፋጦ ይገኛል። ወታደራዊ አዛዦች ቀሳውስቱን ለምልጃ በመላክ የተማረኩት አንድ መትረጌስ፣ 25 ክላሽንኮቸቭ ጠመንጃና ሌሎችም የነፍስ መወከፍ መሳሪያዎች እንዲመለሱላቸው እየጠየቁ ቢሆንም፣ የነጻነት ሃይሎች ግን የቀሳውስቱን ሽምግልና አልተቀበሉትም። ወታደሮች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ፣ የታሰሩት በሙሉ እንዲፈቱ የሚሉና በርካታ ቀድመ ሁኔታዎችን ያቀረቡት እነዚህ ሃይሎች፣ መሳሪያ በሃይል ለመንጠቅ ከተሞከረ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ይከተላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። በሰላማዊ መንገድ ሲካሄድ የነበረው በአማራ አካባቢ የሚካሄደው የነጻነት ተጋድሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃይል የተለወጠ ሲሆን፣ የተለያዩ አካባቢ ወጣቶች ራሳቸውን እያደራጁ የነጻነት ትግሉን ቀጥለዋል።
በሌላ በኩል አገዛዙ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ እስርና አፈናው አሁንም እንደቀጠለ ነው። የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከ11 ሺ በላይ ዜጎችን ማሰሩን ዛሬ ሲያስታውቅ፣ ሌሎች ወገኖች ግን ቁጥሩን በእጅጉ ቀንሶ ማቅረቡን ይገልጻሉ።
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በአማራ፣ ኦሮምያና ደቡብ ክልሎች የታየውን ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት 11 ሺ 607 ሰዎችን ማሰሩን ሲያስታውቅ፣ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው የእስረኞች ቁጥር ከ40 ሺ በላይ ነው ይላሉ። የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ ቀደም ብሎ ባወጣው መረጃ ከ40 ሺ ያላነሱ ዜጎች በኦሮምያ አካባቢ ብቻ መታሰራቸውን ገልጿል። በአማራ አካባቢ በብርሸለቆና በተለያዩ እስር ቤቶች ከ 10 ሺ ያላነሱ ዜጎች ሳይታሰሩ እንደማይቀር መረጃዎች ያመለክታሉ።
አገዛዙ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከዚህ ቀደም ፈታሁዋቸው ያላቸውን ከ2 ሺ በላይ ዜጎች አልጠቀሰም። በአዋሽ ማእከል ከፊንፊኔ ዙሪያ፣ ከሰሜን ሸዋ፣ ከምስራቅ ዞኖች 1 ሺ 174፣ ከጦላይ ፣ ከቄለም ወለጋ፣ ከአርሲ፣ ከምዕራብ አርሲ፣ ከምስራቅ ሰዋ ዞኖች፣ 4 ሺ 329፣ ከዝዋይ አላጌ ማእከል፣ ከጎጂ ዞኖች 3 ሺ 48፣ በዲላና ይርጋለም፣ ከጌዲዮ አካባቢ 2 ሺ 114፣ በባህርዳር ማእከል፣ ከሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ከምስራቅ ጎጃም፣ ከአዊ ዞኖች 532 እንዲሁም በአዲስ አበባ ማእከላዊ 410 ዜጎች ታስረዋል።
በብርሸለቆ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ጫካዎች ፣ በባህርዳር መኮድ፣ በጎንደር ባዘዞ ወታደራዊ ካምፖች፣ በደዴሳ እና ሌሎችም አካባቢዎች የታሰሩት አልተገለጸም።
የእስረኞችን ቁጥር ለመቀነስ በሚመስል መልኩ መረጃው ከመውጣቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከባህርዳር እና አካባቢዋ የታሰሩትን ወጣቶችና ነጋዴዎች ወደ ብርሸ ለቆ ወታደራዊ ካምፕ ለመውሰድ ጉዞ ከተጀመረ በሁዋላ እሰረኞች እንዲመለሱ ተደርጓል።