የካቲት ፳፫ ( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 6 ቀበሌ 11የቤት ቁጥር 207 ተክለሃይማኖት አካባቢ የሚገኘው የታዋቂው የሃይማኖት አባት አለቃ አያሌው ታምሩ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ በርካታ ቤቶች እንደሚፈርሱ ታውቋል። በጽኑ ታመው አልጋ የያዙት ባለቤታቸው እና ልጆቻቸውን ቤታቸውን በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያፈርሱ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ከ50 ዓመታት በላይ ጎጆ ቀልሰው የኖሩበትን የሊቀ ሊቃውንት አያሌው ታምሩን መኖሪያ ቤት በቅርስነት መዝግቦ እንዲጠበቅ ከማድረግ ይልቅ፣ የፀሎት እና የምርምር ክፍላቸውን ሳይቀር እንዲፈርስ ለማድረግ የሚደረገው እሩጫ አግባብ አለመሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል።
ምትክ መኖሪያ ሳይዘጋጅላቸው መኖሪያ ቤቶቻቸው በላያቸው ላይ እንዲፈርሱባቸው ውሳኔ የተላለፈባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።