ሐምሌ ፲፩(አስራ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዘወትር አርብ የሚደረገውን ስግደት ተከትሎ ተቃውሞ ሊያስነሱ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩ ከ10 ያላነሱ የወለድያ ከተማ ነዋሪዎች ታስረው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ከታሰሩት መካከል ኢብራሂም ገበየሁ፣ ከድር ሙሀመድ፣ ወ/ሮ ሀያት ይማም፣ ወ/ሮ ነሲሳ አህመድ፣ ወ/ሮ ሀያት አህመድ ይገኙበታል። ወ/ሮ ሀያት አህመድ ሁለት ወር ያልሞላት አራስ ስትሆን፣ ወደ እስር ቤት የተወሰደችውም አዲስ ከተወለደው ህጻኗ ተለይታ ነው።
በፖሊስ ጣቢያው አካባቢ የተሰባሰበው ህዝብ ” ቤተሰቦቻችንን ፍቱልን” በማለት ከሰአት በሁዋላ በፖሊስ ጣቢያ አካባቢ በመሰባሰብ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ በፖሊስ ተባረዋል።
የአካባቢው ሙስሊሞች “መሄጃ አጣን” በማለት ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የወልድያን ፖሊስ ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።