በወልድያ ታዋቂ ባለሃብቶች ታሰሩ

ኀዳር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በከተማው ከሚገኙና በአብዛኛው የገዢው ፓርቲ ዋነኛ ደጋፊ ባለሃብቶች ተብለው ከሚታወቁት መካከል 14 ቱ በአራጣ ማበደር ወንጀል ተከሰው ከሶስት ቀናት በፊት ታስረዋል።
ከተያዙት ባለሃብቶች መካከል አቶ ስማቸው፣ አቶ ዘገየ መላኩ፣ ዶ/ር በቀለ፣ ሞላ ጌታሁን፣ አውዱ፣ ኪዳኔ ካህሳይ፣ አበበ ደመቀ፣ አቶ እስራ፣ ፖለስ ጌታው አበሬ፣ እንዲሁም አቶ ካሳሁን ይገኙበታል።
ባለሀብቶቹ የብአዴን ባንክ ከሆነው አባይ ባንክ በብዙ ሚሊዮኖች የመቆጠር ገንዘብ በመውሰድና አራጣ በማበደር ባንኩን ለኪሳራ መዳረጋቸው ለእስር ዳርጓቸዋል። አንዳንዶቹ ባለሃብቶች ከባለስልጣናቱ ጋር በመመሳጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነርነት ደረጃ የደረሱ ሲሆን፣ ለብአዴን የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለእስር ያበቃቸውም የድርጅቱን ባንክ እስከማክሰር በመድረሳቸው ሊሆን እንደሚችል ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።