በወልዲያ የተቀሰቀሰው የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት የስራ ማቆም አድማ ወደሌሎች ከተሞች መስፋፋቱ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2008)

በወልዲያ ከተማ የተጀመረው የአሽከርካሪዎች የመኪና ባለቤቶች የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።

ትናንት ከቀትር በኋላ የተጀመረው አድማ ዛሬ ሌሎች የሰሜን ወሎ ከተሞች መቀላቀላቸውን ያገኘነው መረጃ የመለክታል።

በደሴ ዛሬ በስፋት የተጀመረ ሲሆን ኮምቦልቻ ውርጊዛ፣ ውጫሌ፣ ቆቦና አላማጣ ከተሞችም በተመሳሳይ የአሽከርካርዎች አድማ ተመቷል። በወልዲያ የመንግስት ባለስልጣናት ማስፈራሪያና ማታለያ የተንጸባረቀበት ስብሰባ ለተሽከርካሪ ባለሃብቶች አዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም፣ ባለሃብቶቹ ለአሽከርካሪዎች አጋርነታቸውን በማሳየት የመንግስት ባለስልጣናትን ማስፈራሪያ ውድቅ አድርገዋል።

ዛሬ በአብዛኛው በሰሜንና የደቡብ ወሎ ከተሞች አድማው የተመታ ሲሆን መናሓርያዎችም ጭር ብለው መዋላቸው ከስፍራው የደረስን ዜና ያመለክታል።

በጎንደር ከተማም ዛሬ ጠዋት ታክሲዎች አድማ መትተው እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል። በአዲስ የትራፊክ ህግና በነዳጅ ዋጋ ላይ በማነጣጠር የተጀመረው ሃገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ከአንድ ወር በፊት በደቡብ ኢትዮጵያ ሆሳዕና የተካሄደ ሲሆን መንግስት በማፈግፈግ ለጊዜው ህጉን ማዘግየቱ የሚታወስ ነው። ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ በአዲስ አበባ መጠነ ሰፊ የታክሲዎች አድማ ተደርጎ የወጣው ህግ እንዲዘገይ በመንግስት ውሳኔ ተላልፏል።

በኦሮሚያ በባሌ በአርሲ በአምቦ፣ ወሊሶ አዳማና ሌሎች ከተሞች ሃገር አቀፍ የአሽከርካሪዎች አድማ በስፋት እየተደረገ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።