በወልዲያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ –ጥር 14/2010)

በወልዲያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለ3ኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።

ትላንት ምሽቱን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ንብረት ላይ ርምጃ ሲወሰድ እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ዛሬ ጠዋት ነዋሪው በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ተቃውሞ ማድረጉም ተመልክቷል።

የአጋዚ ወታደሮችን ተኩሶ የገደለው ወጣት የቀብር ስነስርዓት በተቃውሞ ታጅቦ ተከናውኗል።

ዛሬም በአጋዚ ወታደሮች ግድያ መፈጸሙ ታውቋል።

ተጨማሪ ሃይል ወደ ከተማዋ ያስገባው የህወሃት አገዛዝ በወታደራዊ ሃይል የህዝቡን ተቃውሞ ለማስቆም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑም ተገልጿል።

የህዝቡ ቁጣ እየጠነከረ መጥቷል። ወደ ወልዲያ የሚያስገቡ መንገዶች ተዘግተዋል።

በህወሃት አገዛዝ ሰራዊት የተገደሉትን ለመቅበር በወጣው ህዝብ ላይ ተጨማሪ ጥቃት መፈጸሙ ያስቆጣው ህዝብ ወደቤቱ መግባት አልቻለም። ዛሬም አደባባይ ወጥቷል።

እንደሰሞኑ ባይሆንም ዛሬም በወልዲያ ተቃውሞ መደረጉን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

የአጋዚ ተጨማሪ ሃይል መግባቱም ነዋሪውን ይበልጥ ወደ ተቃውሞ እያስገባው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

የዛሬው ተቃውሞ ከቀትር በኋላ ጋብ ያለ ቢመስልም ዳግም ሊያገረሽ ይችላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ትላንት እስከምሽት አራት ሰዓት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በወልዲያ በተለያዩ አባቢዎች ከህወሀት አገዛዝ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ንብረት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዛሬም ግድያ ተፈጽሟል።

በቅዳሜው ተቃውሞ ከህወሃት ደጋፊ ቤት ባገኘው መሳሪያ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ የአጋዚ ወታደሮችን የገደለውና ራሱንም ያጠፋው ወጣት የቀብር ስነስርዓት ተፈጽሟል።

በዚህን ወቅትም ተቃውሞ ተቀስቅሶ ሁለት ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ኢሳት ግድያውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት እየሞከረ ነው።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ያነጋገርናቸው ገልጸዋል።

የንግድ እንቅስቃሴው ቆሟል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ከቀትር በኋላ መንገዶች ላይ የሚታይ ነገር የለም። ከወልዲያ የሚያስወጡና የሚያስገቡ መንገዶች እንደተዘጉ ናቸው።