በወልዲያ ከ7 በላይ ሰዎች የተገደሉት ወጣቶች ባስነሱት ግጭት ምክንያት ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2010)

በወልዲያ በቃና ዘገሊላ በዓል ላይ ከ7 በላይ ሰዎች የተገደሉት የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ወጣቶች ባስነሱት ግጭት ምክንያት ነው ሲሉ የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ገለጹ።

መምሪያ ሃላፊው ኮማንደር አማረ ጎሹ የአካባቢው ታጣቂዎች ትዕግስታቸው በማለቁ ርምጃውን ለመውሰድ ተገደዋል ብለዋል።

ወጣቶቹ ግን በጭፈራ ከመቃወም ውጪ የፈጸሙት ነገር አለመኖሩን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ችግር ቢኖር እንኳ የሰው ሕይወት መጥፋት አልነበረበትም ነው ያሉት።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአካባቢው ተገኝተው በሰበቡ የታሰሩ ወጣቶች እንዲለቀቁ ማድረጋቸው ተነግሯል።

በወልዲያ በጥምቀት በዓል የሚካኤል ንግስ ስነስርዓት ሲካሄድ ሕዝቡ በዝማሬና በጭፈራ ታቦቱን በማጀብ ላይ ነበር።

የአካባቢው የአይን እማኞች እንደገለጹት ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ጭፈራ ላይ እያለ የጦር መሳሪያ የታጠቁ የአገዛዙ ወታደሮች ታዳሚውን ሲያጅቡ የሚጨፍሩ ወጣቶችን ለማስቆም ይሞክራሉ።

ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ የያዙ ወጣቶችን ለመንጠቅ እንደሞከሩም ነው የተነገረው።

በዚህ ሳቢያ በተፈጠረ ግጭት ታዲያ ታጣቂዎች የእሩምታ ተኩስ በመክፈት ከ7 በላይ ሰዎች ሲገድሉ 15 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል።

7 ሰዎች መሞታቸው በክልሉ መንግስት የታመነ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ግን ከዚህም እንደሚልቅ ነው የተገለጸው።

ዛሬ ብቻ 2 ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል።

ጅምላ ግድያውን አስመልክቶ የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መመሪያ ሃላፊ ኮማንደር አማራ ጎሹ ለአማራ ቴሌቪዥን እንደገለጹት ግጭቱ የተቀሰቀሰው የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ባላቸው ወጣቶች ነው።

ኮማንደሩ እንደሚሉት የአካባቢው ታጣቂዎች ትዕግስታቸው በማለቁ ርምጃውን ለመውሰድ ተገደዋል።

ይህንኑ ተከትሎም በማግስቱ ጨምሮ በነበረው ግጭት ተሽከርካሪዎች፣ሆቴሎችና የተለያዩ የንግድ መደብሮች ወድመዋል ነው ያሉት።

የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት የንብረት ጉዳቱ የደረሰው ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ባላቸውና በሕዝቡ ላይ ችግር ሲፈጥሩ በነበሩ ባለንብረቶች ላይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ችግር ቢኖር እንኳ የሰው ሕይወት መጥፋት አልነበረበትም ሲሉ በኮማንደሩ ሃሳብ እንደማይስማሙ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በአካባቢው ተገኝተው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ወጣቶች እንዲለቀቁ ማድረጋቸውም ተነግሯል።

የወልዲያውን ግጭት ተከትሎ ከፌደራል መንግስትም ሆነ ከሃይማኖት አባቶች ዘንድ እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።