በወልዲያ በአገዛዙ ታጣቂዎች የተፈጸመው ጅምላ ግድያ ተወገዘ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2010)

በወልዲያ በጥምቀት በዓል ማግስት በቃና ዘገሊላ በዓል ላይ በአገዛዙ ታጣቂዎች የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት በጽኑ አወገዙ።

ፓርቲዎቹና የሲቪክ ማህበራቱ ግድያውን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት በሕወሃት/ኢሕአዴግ የሚመራውን አገዛዝ ለማስወገድ ሕዝቡ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።

በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደው የጸረ ሕወሃት ትግልን ማቀናጀት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በአገዛዙ ፋሽስታዊ ርምጃ ሕይወታቸው ላለፉ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።

የእነዚህ ወገኖች ሕይወት የተከፈለውም ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለሰብአዊ ክብር መሆኑንም ነው የገለጸው።

ህይወታቸው ለአገር አንድነት የተከፈለ ዋጋ ስለሆነም ንቅናቄው ለሟቾቹ ያለውን ክብር ገልጿል።

ሕወሐት ከስህተቴ ተምሬያለሁ፣ ሕዝብንም ይቅርታ እጠይቃለሁ በማለት የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋልሁ ቢልም በዚህ ጭፍጨፋ ድርጅቱ ባህሪው የማይለወጥ መሆኑን ማየት ይቻላል ብሏል።

እናም ህወሀትን ማስወገድና ለፍርድ ማቅረብ የቅርብ ግባችን ነው ሲል ንቅናቄው አቋሙን ገልጿል።

የሕወሐትን መወገድና በምትኩ የሸግግር መንግስት ማቋቋምም የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑንም ነው የገለጸው የአርበኞች ግንቦት ሰባት።

የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሐይል ንቅናቄ/አዴሀን/ ግድያውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫም በወልድያ በሕወሐት የተፈጸመው ጅምላ ግድያ በአማራውና በኦርቶዶክስ የክርስትና እምነት ላይ የተፈጸመ ቀጣይና ስልታዊ ዘርን የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው ብሏል።

እናም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሐይል ንቅናቄ/አዴሀን/ በወልድያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ በሀዘን ብቻ የሚያልፈው ሳይሆን በቆራጥ ትግሉና በልጆቹ አጸፋዊ የጸረ ሕወሀት በትር ድርጊቱን እንደሚበቀል ነው የዛተው።

የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ አመራሮቹ አቶ ታዘበው አሰፋ እና አቶ ማተቤ በለጠ ከውጭ ሀገር ወደ ግንባር በመሄድ በትግል ላይ ያለውን ሰራዊት በማበረታት ላይ መሆናቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/ አለም አቀፍ ትብብር ባወጣው መግለጫም በወልድያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ የሚወገዝ ነው ብሏል ።

ኦፌኮ እንዳለው በኢትዮጵያ ያለው ችግር በፖለቲካ፣ በውይይት እና በድርድር እንጂ በወታደራዊ ርምጃ ሊፈታ አይገባም።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ልሳነ ግፉአን የወልቃይት ማህበረሰብ ባወጣው መግለጫም በወልድያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ አውግዟል።

የልሳነ ግፉአን መግለጫ በየደረጃው ያለው የሕዝብ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ሕወሐት ምንም አይነት እርምጃ ቢወስድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ሆነ የሲቪክ ማህብረሰቡ ተቋም በሕወሐት/ኢህአዴግ የሚመራውን አገዛዝ ለማስወገድ ሕዝቡ በጋራ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።

በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደው የጸረ ሕወሐት ትግልን ማቀናጀትም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።