በወልዲያ ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2010)

በወልዲያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉ ታወቀ።

በወልዲያ ሃራ አካባቢ ህዝቡ የወሰደው ርምጃ

 

በዕለቱ ይውል የነበረው የማክሰኞ ገበያም እንዳይቆም ተደርጓል።

የተገደሉት ሰዎች ቁጥ እያሻቀበ ነው። በአልሞ ተኳሽ ከተመቱት ሌላ በስልት ተወግተው ሆስፒታል የገቡ በርካታ ሰዎችም እንዳሉ ይነገራል።

የግጭቱ መንስዔ በበዓሉ ላይ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት የሚያንጸባርቁ ወጣቶች እንደሆኑ በህወሃት አገዛዝ በኩል ተገልጿል።

ለኢሳት ዛሬ በደረሰው መረጃ ግን ከ13 ሰዎች በላይ በግፍ ለተገደሉበት የወልዲያው ጭፍጨፋ መነሻው የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፍ መሆኑ ታውቋል።

የአይን እማኞች ለኢሳት ባደረሱት መረጃ ላይ እንደተገለጸው ከአንድ ወር በፊት በወልዲያ በእግር ኳስ ግጥሚያ ላይ የተፈጠረው ግጭትና ያንንም ተከትሎ ህዝቡ የወሰደው ርምጃ በህወሃት ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ፈጥሯል።

ከመሀል ሀገር ወደ ትግራይ የሚገቡ ምርቶች በዋናነት በወልዲያና ዙሪያዋ የሚተላለፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህዝቡ እየወሰደ ያለውን ያነጣጠረ ጥቃት ለማስቆምና ቂሙንም ለመወጣት ዝግጅት ሲደረግ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ አንስቶ ተጨማሪ ሃይል ወደ ወልዲያ እንዲገባ መደረጉን የሚጠቅሱ ወገኖች የህወሃት አገዛዝ ወልዲያ ላይ ርምጃ ለመውሰድ አቅዶ ተዘጋጅቶ እንደነበረ የሚያረጋግጥ ነው ይላሉ።

ባለፈው ቅዳሜ የሚካዔል ታቦት በሚገባበት ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ላይ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶግራፍ ይዘው የወጡ የህወሃት አባላት ለተፈጠረው ግጭት መንስዔ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፍ በባነር ተዘጋጅቶ በበዓሉ ትዕይንት ላይ መታየቱ የወልዲያን ወጣቶች ማስቆጣቱን የሚጠቅሱት ምንጮች ከዚያን በኋላ ሁኔታው ተባብሶ ጭፍጭፋው መፈጸሙን ገልጸዋል።

የግጭቱን መነሻ በተመለከተ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጠሩት ስብሰባ ላይ የወልዲያ ወጣቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገለጽ የጠየቁ ቢሆንም አቶ ገዱ እስከአሁን ስለጉዳዩ የተነፈሱት ነገር የለም።

በስብሰባው ላይ የአጋዚ ሰራዊት ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ፣ የህወሃት አገዛዝ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ ወጣቶቹ መጠየቃቸውም ታውቋል።

አቶ ገዱ የተጠየቁትን ቃል ከመግባት ውጪ በተግባር ማስፈጸም እንዳልቻሉ ታውቋል።  ለኢሳት በደረሰው መረጃ የወልዲያ ወጣቶች እየታፈሱ ነው።

በስብሰባው ላይ የአጋዚ ሰራዊት ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ፣ የህወሃት አገዛዝ በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርድ ወጣቶቹ መጠየቃቸውም ታውቋል።

አቶ ገዱም የተጠየቁትን ቃል ከመግባት ውጪ በተግባር ማስፈጸም እንዳልቻሉ ታውቋል።

ዘግይቶ በደረሰን መረጃም የመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሃይል እና አድማ በታኞች ከወልዲያ ከተማ እንዲወጡ ተደርገዋል።