በወልዲያና ፍኖተ ሰላም እስር ቤቶች ውጥረት መንገሱ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 18/2010) በወልዲያና ፍኖተ ሰላም እስር ቤቶች ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ።

የምህረት አዋጁ ላይ አልተካተትንም በሚል የተጀመረው ተቃውሞ ቀጥሎ ወልዲያና ፍኖተ ሰላም የሚገኙ እስር ቤቶች ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውም ተሰምቷል።

በፍኖተ ሰላም እስር ቤት የሽመና መስሪያው ቤት መውደሙ ታውቋል። በወልዲያ እሳቱን ለማጥፋት የተጠጋው ነዋሪ በፖሊስ ሃይል መበተኑ ቁጣን አስነስቷል።

በተያያዘ ዜና በቃሊንጢ ሌሊቱን የእስረኞች የድረሱልን ድምጽ ሲሰማ እንደነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የምህረት አዋጁን የአፈፃፀም መመሪያ በመቃወም በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች እስረኞች በጩህትና ቤቶችን በማቃጠል ቁጣቸውን መግለጻቸውን ቀጥለዋል።

በቃሊቲ፡ ደብረማርቆስ፡ አርባምንጭ በአንድ ሌሊት የጀመረው ተቃውሞ ወደሌሎች እስር ቤቶችም ተዛምቷል።

ሌሊቱን በወልዲያና ፍኖተ ሰላም እስር ቤቶች ተቃውሞ ተቀስቅሶ በርካታ ቤቶች በእሳት መጋየታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በቃሊቲ ለሁለተኛ ሌሊት እስረኞች የድረሱልን ድምጽ ማሰማታቸው የተገለጸ ሲሆን የምግብ አድማ መመታቱ ታውቋል።

ዛሬም የጭስ ተኩስ በእስረኞች ላይ መተኮሱን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ወደ እስረኞች ቤተሰቦችም በመተኮስ ከፍተኛ ግርግር ተፈጥሮ እንደነበረ ተገልጿል።

በቂሊንጦ እስር ቤትም የቀጠሮ እስረኞች ወደ ፍርድ ቤት አንሄድም በማለት አድማ መምታታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም እስር ቤት በተነሳው ተቃውሞ የሽመና መስሪያው ቤት ሙሉ በሙሉ ሲወድም እሳቱን ለመቆጣጠር በርካታ ሰዓታት መውሰዱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የተኩስ ድምፅ በተከታታይ ይሰማ እንደነበረ የጠቀሱት ምንጮች ወዲያውኑም የእሳት ቃጠሎ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ለማገዝ ሌላ ተጨማሪ የልዩ ሃይል አድማ በታኝ ታጣቂ እስኳድ መግባቱ ታውቋል።

በወልዲያ እስር ቤትም በተመሳሳይ የእስረኞች ተቃውሞ ተቀስቅሶ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መደረሱን ለማወቅ ተችሏል።

በተቃውሞ ወቅት በተነሳ ቃጠሎ የተወሰኑ ቤቶች መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን ለረጅም ሰዓታት እሳቱን ማስቆም ባለመቻሉ አደጋው የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የወልዲያ ነዋሪ እሳቱን ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ በታጣቂዎች ክልከላ ሊሳካ አልቻለም።

አንቡላንስ ተሽከርካሪዎች ወደ እስር ቤቱ እየገቡ ሲሆን በከተማው መንገዶች ወጣቶች ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበርም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በተያያዘም በመቀሌ ማረሚያ ቤት እሳት ቃጠሎ መነሳቱንና ከዛም ጋር ተያይዞ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል።

እንደ ምንጮቹ ከሆነ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ ሰዎች ደሞ ተጎድተዋል።