ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)
በወልቃይት አዲ-ረመጽ ከተማ የሚገኘ አንድ ሆቴል የአማርኛ ዘፈን በመከፈሩ የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት የሃይል ዕርምጃ በነዋሪዎች ዘንድ አዲስ ውጥረት መቀስቀሱን የከተማዋ ነዋሪዎች ረቡዕ ለኢሳት አስታወቁ።
የትግራይ ክልል ልዩ የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት በዚህ ዕርምጃ የሆቴሉ ባለቤት ልጅ ክፉኛ የድብደባ ድርጊት እንደተፈጸመበትና የከተማዋ ነዋሪዎች ከማክሰኞ ጀምሮ ተቃውሞ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን እማኞች ገልጸዋል።
በአዲ-ረመጽ ከተማ የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ነዋሪዎች በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በመሰባሰብ ስራ እንዲስተጓጎል አድርገው መዋላቸውንም እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ከአመታት በፊት ያነሱት የማንነት ጥያቄ ህጋዊ ምላሽን አላገኘም በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ በአካባቢውና በሌሎች የአማራ ክልል ከተማ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
ነዋሪዎቹ ያቀረቡትን ይህንኑ የማንነት ጥያቄ ተከትሎ በትግራይ ክልል የጸጥታ ሃይሎች የሃይል ዕርምጃ ሲወሰድባቸው መቆየቱን ይገልጻሉ።
በአካባቢው ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ በማለት የጎንደርና ባህርዳር ከተሞች ነዋሪዎች ተቃውሞን እያካሄዱ የሚገኝ ሲሆን፣ የፌዴራል ባለስልጣናት የወልቃይትን ጉዳይ በአማራና ትግራይ ክልሎች በኩል ዕልባት እንዲያገኝ ይደረጋል ሲሉ በቅርቡ አስታውቀዋል።