ኢሳት (መጋቢት 12 ፥ 2008)
ከወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እሁድ በወልቃይት ዳንሻ ግጭት ማስነሳቱን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎም በትግራይ ልዩ ፖሊስና በወልቃይት የታጠቁ ነዋሪዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ማካሄዱንና መንገዶች መዘጋታቸውንም እማኞች አስታውቀዋል።
እሁድ የተቀሰቀሰው ግጭት ሰኞ ድረስ እልባት አለማግኘቱን የተናገሩት ነዋሪዎች፣ ሁለት የዳንሻ የማንነት ኮሚቴ አባላት ለእስር መዳረጋቸውንም እማኞች ለኢሳት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።
“አማራ ነን” ስላልን ብቻ ግድያ እየተፈጸመብን ነው በማለት እየደረሰባቸው ያለን በደል ያስረዱት ነዋሪዎች በአቅራቢያ ባሉ መንደሮች የሚገኙ የወልቃይት ነዋሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ እንደሚገኙም ታውቋል።
ለሁለተኛ ቀን የቀጠለውን የዳንሻ ተቃውሞ ተከትሎም ከዳንሻ ሶሮቆ እና ከዳንሻ ሁመራ የሚወስዱ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ በጎንደርና አካባቢዋ የተሰማሩ የጸጥታ ሃይሎች መንገዱን ለማስከፈት ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካ አለመቻሉን እነዚሁ እማኞች አስታውቀዋል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ሞቶ መገኘቱን አክለው የተናገሩት የዳንሻ ነዋሪዎች፣ ግጭቱ አዲስ ውጥረት ማንገሱንም አስረድተዋል።
ግጭቱ እልባትን ባለማግኘቱ ምክንያትም በነዋሪዎች ላይ የደረሰን ጉዳት በአግባቡ ለማወቅ እንዳልተቻለ የዳንሻ ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አመልክተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በአማራ ክልል ከማንነት ጥያቄ ጋር የተነሳው ተቃውሞ ምክክር ተካሄዶበት ህጋዊ እልባትን አግኝቷል ሲሉ በቅርቡ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።