(ኢሳት ዜና–የካቲት 13/2010)
በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ የተጠራው አድማ ለሰባተኛ ቀን መቀጠሉ ተገለጸ።
የገዢው ፓርቲ አባላት የሆኑ ሁለት ሰዎች አድማውን አስተባብራችኋል ተብለው ታስረዋል።
በእንድብርና በአገና የፌደራል ፖሊስ የሃይል ርምጃ እየተጠቀመ ነው።
የጉራጌ ወጣቶች ጥሪ አድረግዋል።
በወልቂጤ የተጀመረው አድማ ሳምንቱን ደፍኗል።
ዛሬም ወደ እንቅስቃሴ አልገባችም።
ባለፉት ሁለት ቀናት አንዳንድ የንግድ ቦታዎች ተከፍተው የነበረ ቢሆንም ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በኋላ በአድማው የቀጠለችው የወልቂጤ ከተማ ሆቴሎች፣ ንግድ ቤቶች፣ የተዘጉ ሲሆን በከተማዋ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንደተቋረጠ ነው።
ኢሳት ያነጋገራቸው የአድማው አስተባባሪዎች እንደሚሉት የጉራጌ ህዝብ የተጠራቀመውን ብሶትና በደል ከዚህ በኋላ የሚሸከምበት ትከሻ የለውም።
የህዝቡን ፍላጎት እየተከተልን ተቃውሞንና አድማውን እንቀጥላለን ብለዋል።
ትላንት ሁለት የአገዛዙ አባላት አድማውን ታስተባብራላችሁ ተብለው መታሰራቸውም ታውቋል።
ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተውም የጉራጌ ዞን አስተዳደሪ ከአድማው ጀርባ የፓርቲው አንዳንድ አመራሮች ሳይቀር እጃቸው አለበት በሚል ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በርካታ የመንግስት ሰራተኞች በይፋ አድማውን በመቀላቀል ለውጥ እንፈልጋለን የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
በሌሎች የጉራጌ ዞን አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ የተከታተለው የኢሳት ወኪል እንደገለጸው በእንድብርና በአገና በፌደራል ፖሊስ ሃይል አንዳንድ ሱቆች ተከፍተዋል።
በከተሞቹ የአገዛዙ ሃይሎች በብዛት መግባታቸው ታውቋል።
የአድማው አስተባባሪዎች እንደሚሉት በርካታ ወጣቶችን በማሰር አድማውን ለማስቆም በአገዛዙ በኩል እየተወሰደ ያለው ርምጃ ህዝቡን አስቆጥቶታል።
በአማላጅነት መንግስት ለላካቸው የሀገር ሽማግሌዎች ምላሽ የሰጠው የወልቂጤ ነዋሪ፣ የመንግስትን መልዕክት ይዛችሁ አትምጡብን ብሎ እንደመለሳቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከእንግዲህ የምንሰማው የጉራጌ ወጣቶችንና ዘርማዎችን ነው ሲሉም መናገራቸውን የአድማው አስተባባሪዎች ይገልጻሉ።
የጉራጌ ህዝብ ለለውጥ የተነሳና ከዚያ የሚመልሰው ምንም የለም የሚሉት አስተባባሪዎች ሌሎች የጉራጌ ዞን ወረዳዎች አድማውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አድርገዋል።
የጉራጌ ወጣቶች ትግል የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል አካል ነው በማለትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢሊባቦር ቄሮዎች የህወሃት አገዛዝ ያወጣውን የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ጎን በማለትና የአማራ ደም ደሜ ነው ሲሉ በአደባባይ ድምጻቸውን ማሰማታቸው ታውቋል።
በመልዕክታቸውም የኛ ትግል የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር እንጂ የኦሮሞ ሕዝብን ለመገንጠል አይደለም ሲሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።