(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2010)
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ።
የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም መቋረጡ ታውቋል።
በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝባዊ ንቅናቄ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።
በሸካ ዞን ማሻም የስራ ማቆም አድማ ተደርጓል።
በጋምቤላ ከተማ የአድማ ጥሪ ወረቀት ተበትኗል።
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ታቅዶ የነበረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ መጀመሩ ታውቋል።
የወልቂጤ ነዋሪ የተጠራቀመውን ብሶትና ምሬቱን ያባባሰውን የሆስፒታል ግንባታ መቅረት ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ዝሬ ሱቆችንና መደብሮችን በመዝጋት ከተማዋን ከማንኛውም አይነት የንግድ እንቅስቃሴ በመግታት ቀጥሏል።
ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው ወልቂጤ ጭር ብላለች።
መንገዶች ላይ ተሽከርካሪ አይታይም።ሰው በቤቱ ተቀምጧል።
ወደ ሌሎች የጉራጌ ዞን ከተሞች ሊዛመት እንደሚችልም እየተነገረ ነው።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን የሚያሳዩ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰውታል።
ከጎንደር ወደ ሽሬ የሚወስደው መንገድ አድርቃይ ላይ ዘግቷል።
በደጀን ከ300 በላይ ተሽከርካሪዎች ከትላንት ጀምሮ መቆማቸው ታውቋል።
የአባይ በረሃ በመከላከያ ሰራዊት ተጨማሪ ሃይል እየተጠበቀ ነው።
ተሽከርካሪዎች በአባይ ድልድይ መሻገር እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአዴት-ኮምቦልቻ የንግድና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መቆሙ ታውቋል።
ወደ ሱዳን ነዳጅ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችም ከትላንት ጀምሮ ከእንቅስቃሴ ውጪ መሆናቸው ተገልጿል።
ከጋይንት ጀምሮ ወደ ወሎ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል።
በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን ማሻ ከተማ የስራ ማቆም አድማ መደረጉን የአገዛዙ ደጋፊ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የኦሮሚያው እንቅስቃሴ ያነቃቃት ማሻ አድማ ማድረጓን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
በጋምቤላ የአድማና የተቃውሞ ጥሪ ወረቀት የተበተነ ሲሆን ሕዝቡ ለለውጥ እንዲነሳ ተጠይቋል።