(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 7/2010) በወልቂጤ ህዝቡ ተቃውሞ በማድረግ ላይ መሆኑ ታወቀ።
የመከላከያ ሰራዊትና ፌደራል ፖሊስ ወጣቱን በማፈስ እያሰሩ ቢሆንም ነዋሪው ቁጣውን በመግለጽ ላይ ነው።
በእስከሁኑ ተቃውሞም ሶስት ሰዎች ተገድለዋል። ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው በተለያዩ የህክምና ማዕከላት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ከ30 በላይ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን አራት የመንግስት ተሽከርካሪዎችም በእሳት መጋየታቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል በሀዋሳ በተነሳው ግጭት ከ30 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ዛሬ በአንዳንድ የከተማዋ አከባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸውም ታውቋል።
ማክሰኞ ድንገት የተጀመረው የእርስ በእርስ ግጭት ወደአጠቃላይ ቀውስ ተሻግሯል።
በህወሀት አገዛዝ በተተከለው ብሄር ተኮር መዋቅር ምክንያት ውዝግብ ተለይቶት የማያውቀው የጉራጌ ማህበረሰብ በማንነት ጥያቄ ሰበብ ወደ ከፋ የእርስ በእርስ ግጭት ያመራል የሚለው ስጋት እየተሰማ ነው።
የክልል መዋቅር ይገባናል የሚል የመብት ጥያቄም ከሰሞኑ ግጭት ጋር በተያያዘ እየተነሳ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የቀቤና ማህበረሰብ የጉራጌ ተወላጆች ከአካባቢው ይውጡ በሚል በመለስተኛ ውዝግብ የተጀመረው ግጭት የሶስት ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱም ታውቋል።
ትላንት የተገደለን ወጣት ቀብር ለመፈጸም የወጣው የወልቂጤ ነዋሪ በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ትላንት ሌሊት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የፌደራል ፖሊሶች ቤት ለቤት ሲያስሱ ማደራቸውም ታውቋል።
በተለይ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ አፈሳ በማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ማሰራቸው ተገልጿል። ዛሬም አፈሳ ሲካሄድ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በአገዛዙ ታጣቂዎች በተወረረችው ወልቂጤ ነዋሪው ዛሬ በፈጸመው የቀብር ስነስርዓት ላይ ተቃውሞውን በማሰማትየኢትዮጵያ ህዝብ ለስርዓት ለውጥ እንዲነሳ የሚጠይቁ መፈክሮችን ሲያሰማ ነበር ተብሏል።
በቀብር ስነስርዓቱ ላይ ከታጣቂዎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ታውቋል።
ከማክሰኞ ጀምሮ ወደ ወልቂጤ የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸው ተሽከርካሪዎች ከከተማዋ መውጪያ በተለያዩ መስመሮች መቆም ግዴታቸው ሆኖ ሶስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።
የጉራጌ ተወላጆች መኖሪያ ቤቶች ተመርጠው መቃጠላቸውንም ለኢሳት ቃለመጠይቅ የሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በትንሹ 30 ቤቶች ተቃጥለዋል። ነዋሪው በቁጣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከአራት በላይ ተሽከርካሪዎች በእሳት ተያይዘው መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን የመንግስት ንብረቶች ላይ የሚደረገው ጥቃት እየተጠናከረ መምጣቱም ታውቋል።
በሌላ በኩል የጉራጌ ወጣቶች እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በሚል የፊታችን ቅዳሜ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራታቸውን አስታውቀዋል።
ዘርማ በሚል የሚጠሩት የጉራጌ ወጣቶች ቅዳሜ የተጠሩትን የተቃውሞ ሰልፍ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉትና ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ በማድረግ ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጨምበላላ ከመከበሩ ጋር ተያይዞ የተነሳው ሁከትና ብጥብጥ ዛሬም በተወሰኑ የከተማዋ አካባቢዎች መከሰቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የሲዳማ ዞን የክልል መዋቅር ይሰጠው በሚል ጥያቄ የተጀመረው ተቃውሞን ለፖለቲካ ፍጆታ ባዋሉ አንዳንድ ግለሰቦች ጠብ ጫሪነት የተነሳው ግጭት ብሄር ተኮር ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን ሱቆችና መደብሮች እንዲዘረፉ ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል።
የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪንና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መኖሪያ ቤቶችን ለማጥቃት ከተደረገው ሙከራ ጋር በተያያዘ 30 ሰዎች መታሰራቸው ታውቋል።
የሀዋሳ ቄራ ድርጅት በግጭቱ ምክንያት ስራ በማቆሙ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ የስጋ አቅርቦት እንዳልነበረ የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።