በወላይታ ዞን አረካ የሚገኝ አንድ የገበያ ቦታ መቃጠሉ ተነገረ

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2009)

በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ አረካ የሚገኝ አንድ የገበያ ቦታ መቃጠሉ ተነገረ።

የቃጠሎው ምክንያት በውል ባይታወቅም በህዝቡ ውስጥ ከንግድና ከአስተዳደር በደል የመነጨ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የገበያ ቦታው እና በዚያው የነበሩ ሱቆች በደህዴን ካድሬዎች እና በአቶ ሃይለማሪያም ደጋፊዎች የተያዙ ነበሩ። በዚሁ ሳቢያ ወጣቶች የስራ ዕድል ባላገኙበት ሁኔታ ጥቂቶች ተጠቃሚ መሆናቸው በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ምሬት መፍጠሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። በቃጠሎው ስለደረሰው የጉዳት መጠን የታወቀ ነገር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ለምርጫ በተወዳደሩበት አረካ መቶ በመቶ አሸናፊ ሆነዋል በተባለበት ጊዜ አንድም ሰው ለተፎካካሪያቸው ድምፅ አልሰጠም መባሉ ይታወሳል።

በዚህ ውጤት ተፎካክረው እና ቤተሰቦቹ ወይም ደጋፊዎቹ ምንም ድምፅ አልሰጡትም የሚለው የምርጫ ቦርድ ሪፖርት በህዝቡ ዘንድ መሳለቂያ እንደነበር አይዘነጋም።

በወላይታ አረካ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ህዝቡን ወክለው ከተመረጡና ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ መራጮች ዞር ብለው አይተዋቸው እንደማያውቁ ታዛቢዎች ይናገራሉ።