በወለጋ ሻምቡ አፈሳ እየተካሄደ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 27/2010)

በወለጋ ሻምቡ በቅርቡ ከተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ አፈሳ እየተካሄደ መሆኑን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አስታወቀ።

ከትላንት ምሽት ጀምሮ በርካታ የሻምቡ ነዋሪዎች ታፍሰው ተወስደዋል።

በተያያዘ ዜና በምዕራብ ሸዋ ሻሸመኔ አካባቢም ግጭት መፈጠሩ ታውቋል።

በሀረሪ ክልል ኤረር ወረዳ የፌደራል ፖሊስ አንድ አርሶአደር መግደሉን ተከትሎ ውጥረት መንገሱን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

ባለፈው እሁድ በሻምቡ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ለኢሕአዴግ የቅዳሜው መግለጫ ምላሽ ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ተወስዷል።

እሳትና ጭድ፣ መርህ አልባ ግንኙነት እየተባለ በሕወሃት አገዛዝ ተቃውሞ የቀረበበትን የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ወዳጅነት ወደ ሌላ ምዕራፍ መሻገሩን ለማሳየት የሻምቡ ነዋሪዎች የአማራ ጠላት የኦሮሞ ጠላት ነው የሚል መፈክር ይዘው መውጣታቸው የሚታወስ ነው።

ይህ የህዝብ አንድነት ያስቆጣው የሕወሃት አገዛዝ በሻምቡ ነዋሪዎች ላይ የበቀል ርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ነው ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

ከትላንት ምሽት ጀምሮ የአጋዚ ሃይል በተለይም ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ አፈሳ ማድረጉ ተገልጿል።

ምን ያህል ወጣቶች እንደታፈሱ የታወቀ ነገር የለም።

በአዲስ አበባ የሕወሃት አገዛዝ እስረኛን አፈታለሁ እያለ በሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መጠነ ሰፊ አፈሳ ማካሄዱ ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉ የኦፌኮ አመራሮች ገልጸዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት የሻምቡ ተቃውሞ በሕወሃት ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥን በመፍጠሩ እነ ለማ መገርሳን አሁንም መቆጣጠር እንችላለን በሚል በሕወሃት በኩል የተወሰደ ርምጃ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ትላንት በሀረሪ ክልል ኤረር ወረዳ በፌደራል ፖሊስ አንድ አርሶ አደር በጥይት መገደላቸውን ተከትሎ ቁጣ መቀስቀሱ ታውቋል።

አርሶአደሩ የተገደሉት በኡላንኡላ ቀበሌ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ በበርካታ ጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ማድረጉንን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በአካባቢው የሕዝብ ተቃውሞ እንዳይቀሰቀስ ተጨማሪ ሃይል እንዲገባ መደረጉም ታውቋል።

የተገደሉት አርሶ አደር አስከሬን በሆስፒታል የሚገኝ ሲሆን ቤተሰብ እንዲሰተው ቢጠይቅም መከልከሉን በመረጃው ላይ ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሻሸመኔ አቅራቢያ ግጭት መቀስቀሱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ልዩ ስሙ መልካኦዳ በተባለ አካባቢ የተቀሰቀሰው ግጭት መንስኤው ምን እንደሆነ ባይታወቅም ከትላንት ጀምሮ በነዋሪው ዘንድ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን ለማወቅ ተችሏል።