ኢሳት (ጥቅምት 27 ፥ 2009)
በኳታር የሚኖሩ ከሁለት ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ሃገሪቱ በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገችው የህገ-ወጥ ስራተኞችን የማስወጣት ዘመቻ ከኳታር ሊወጡ መሆኑን ተነገረ።
የኳታር መንግስት በቅርቡ ያወጣው አዲስ ህግ በቀጣዩ ወር የሚተገበር በመሆኑ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የበርካታ ሃገራት ህገወጥ የተባሉ ሰራተኞች ህጋዊ እምርጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል የኳታር የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ይኖራሉ የተባሉ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች በተሰጠው የሶስት ወር የጊዜ ገደብ በፈቃደኝነት በመመዝገብ ከኳታር እንዲወጡ ትዕዛዝ መተላለፉን የኳታር ትሪቡዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
ከ2ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በኳታር በህገወጥ መንገድ ይኖራሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ እነዚሁ ኢትዮጵያውያን በቀጣዩ 40 ቀናት ውስጥ መውጣት እንዳለባቸው ለመረዳት ተችሏል።
በኳታር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ እስካሁን ድረስ ወደ 117 ኢትዮጵያውያን ብቻ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በፈቃደኝነት ምዝገባ ማካሄዳቸውን ለኳታር መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ይሁና በርካታ ህገወጥ የተባሉ ኢትዮጵያውያንንና የሌላ ሃገር ዜጎች አሰሪዎቻቸው የአውሮፕላን ትኬት ሊሰጧቸው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ለችግር መዳረጋቸው ኳታር ትሪቢዩን ጋዜጣ አስነብቧል።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁት በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኮንሱላር ሚኒስትር አቶ ሽብሩ ማሞ ኤምባሲው የአውሮፕላን ቲኬትን ወጪ ለመሸፈን በጀት እንደሌለው ለጋዜጣው ተናገረዋል።
ሃገሪቱ ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ በቀጣዮቹ 40 ቀናቶች ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን ቀነ-ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት በፈቃደኝነት ከኳታር የማይወጡ ህገወጥ የተባሉ ሰራተኞች ከፍተኛ ቅጣት ይጣልባቸዋል ተብሏል።
በኳታር በብዙ ሺ የሚቆጠር ዜጋ ያላት ፊሊፒንስ በበኩላ በአዋጁ ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ ዜጎቿን ከሃገሪቱ ለማስወጣት ዘመቻን እያካሄደች እንደሆነ ገልጻለች።