በኮንቴነር ውስጥ ሆነው ሲጓዙ የነበሩ 33 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ዛንቢያ ውስጥ ተያዙ

ግንቦት ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዛንቢያ የስደተኞች ጉዳይ በሕገወጥ መንገድ በኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በጉዞ ላይ የነበሩ 33 ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ስደተኞችን መያዙን አስታውቋል።
ካፉ ከተማ አቅራቢያ በካርጎ ኮንቴነር ተሸሽገው ሲጓዙ የነበሩት ስደተኞች ማንነታቸውን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ፓስፓርትና ሰነድ አለመያዛቸውን የስደተኞች ጉዳይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ናማቲ ኒሺንጋ አስታውቀው ስደተኞቹን ጭኖ ሲያጓጉዝ የነበረው የመኪናው አሽከርካሪ ሳይያዝ ማምለጡንና ስደተኞቹ ተይዘው ሉሳካ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙም አክለው ገልጸዋል።
ስደተኞቹ እድሜያቸው ከ15 እስከ 25 ዓመት ያሉ ወጣቶች መሆናቸንና 43 የሚሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በሉዋንግዌይ አውራጃ በኩል በእግራቸው ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን ዛንቢያ ዴሊ ሜይል የስደተኞች ጉዳይን ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል።