በኮንሶ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 2/2010) የኮንሶ ህዝብ የመብት ጥያቄውን ካነሳበት ጊዜ ጀምሮ ከ200 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ተገለጸ።

የተገደሉት ሰዎች ስም ዝርዝርም ይፋ ሆኗል።

ፋይል

የኮንሶን ህዝብ የመብት ጥያቄ የሚያስተባብሩ አካላት ለኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪል ካውንስል በላኩት ሪፖርት ላይ የዞን መዋቅር መብት በመጠየቅ የተጀመረውን ተቃውሞ ለማፈን የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል የወሰዱት የግድያ፣ የማሰቃየትና ሌሎች ርምጃዎች በዝርዝር ቀርበዋል።

ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በጉዳዩ ተጠያቂ የሚሆኑ የመንግስት ባለስልጣናትና ወታደራዊ አዛዦች ስም ዝርዝርም በሪፖርቱ ተመልክቷል።

የኮንሶ ልዩ ወረዳ መዋቅሩ ፈርሶ ከሌሎች የደቡብ ክልል ወረዳዎች ጋር ተጨፍልቆ የሰገን ህዝቦች ዞን በሚል አዲስ መዋቅር እንዲካለል መደረጉን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ መቋጪያ አላገኘም።

በቋንቋና በማህበራዊ ግንኙነት ከማንመሳሰላቸው ወረዳዎች ጋር በአንድ ዞን ስር እንድንጠቃለል መደረጉ ተገቢ አይደለም የሚለው ተቃውሞ የጀመረው አዲሱ ዞን ከተካለለ ከአምስት አመት በኋላ ነበር።

በእነዚህ ዓመታት የኮንሶ ህዝብ ጥያቄውን በተለያዩ መንገዶች ሲያቀርብ ቢቆይም ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።

እንደኢትዮጵያኑ አቆጣጠር በ2008 ዓመተ ምህረት የኮንሶ ህዝብ ተቃውሞ በማሰማት ጥያቄውን ማቅረብ ጀመረ።

ባለፉት 3 ዓመታት በአከባቢው ሰላም ያጣ ህዝብ በከፍተኛ ቁጥር የተፈናቀለበት፣ መንግስታዊ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው የቆሙበት ሆኗል።

የህወሀት አገዛዝ ጥያቄውን በሀይል ለማፈን በኮንሶ ህዝብ ላይ ሰራዊቱን በማዝመት ከግድያ አንስቶ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ኢሳት በተደጋጋሚ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የኮንሶን ህዝብ የመብት ጥያቄ የሚያስተባብሩ አካላት ሰሞኑን ያጠናቀሩት ሪፖርት ለኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪል ካውንስል ደርሷል።

ኢሳት ያገኘው የአስተባባሪዎቹ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

በስም ዝርዝር፣ በመኖሪያ አድራሻቸው፣ በዕድሜና በጾታ ተገልጾ የተጠናቀረው ሪፖርት ላይ የህወሀት አገዛዝ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና፡ የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ግድያውን እንደፈጸሙ ተገልጿል።

በሪፖርቱ እንደተዘረዘረው የህወሀት አገዛዝ ሃይሎች በግድያ፣ በማሰቃየት፣ ቤት በማቃጠል፣ በዘረፋና መሰል ተግባራት ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል።

ከተገደሉት በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በህወሀት ታጣቂዎች ድብደባና ማሰቃየት ተፈጽሞባቸዋል።

በስም የተዘረዘሩ 70 ሰዎች በአልታወቁ ቦታዎች ታስረው እንደሚገኙም በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ኤች አር 128 የተባለውን ረቂቅ ሰነድ በተመከተ እንቅስቃሴ ለሚያደርገው የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪል ካውንስል የተላከው ሪፖርት በህወሀት አገዛዝ የተፈጸሙ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም በዝርዝር ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህም መሃል ተቃውሞ ባነሱ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ እንዳይደርስ ማድረግ፣ ወፍጮ ቤቶችን መዝጋት፣ በገጠርና ከተማ የሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ፣ ህብረተሰቡ ቀዬና መንደሩን ትቶ እንዲሰደድ ማስገደድ እንደሆኑ ተጠቅሷል።

ሪፖርቱን አጠናቅረው የላኩት አስተባባሪዎች እንደገለጹት በኮንሶ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ላለው መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አንስቶ እስከ ቀበሌ አመራር ድረስ ተጠያቂ ናቸው።

የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግስት ባለስልጣናትና ወታደራዊ አመራሮች በሪፖርቱ ላይ በስም ተዘርዘረው ቀርበዋል።

መከላከያ ሰራዊቱን በማሰማራት ከፍተኛ ስቃይ የፈጸሙት የህወሀት ወታደራዊ አዛዦች ጄነራል መሰለ እና ኮሎኔል መብራሃቱ ከሌሎች አመራሮች ጋር ተጠቅሰው በግድያው ተጠያቂ መሆናቸው ተገልጿል።

አሁንም በኮንሶ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግድያና ስቃይ መቀጠሉን የገለጹት ሪፖርቱን ያዘጋጁት አስተባባሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስላቸውም ጥሪ አድርገዋል።