በኮንሶ በርካታ ሰዎች ከቀያቸው ተሰደዱ፣ በርካቶች ታሰሩ

ኢሳት (መጋቢት 12 ፥ 2008)

በቅርቡ በደቡብ ክልል በኮኖሶ አካባቢ የተነሳውን አስተዳደራዊ ጥያቄ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከቀያቸው መሰደዳቸውንና ወደ 170 ሰዎች አካባቢ በኮንሶ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ታስረው እንደሚገኙ ከቀያቸው የተሰደዱ ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።

በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ የፌዴራልና የክልሉ ልዩ ሃይሎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የገለጹት የአካባቢው ተወላጆች ከ80 የሚበልጡ ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው ተሰደው እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ ማንነታቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት እነዚሁ የአካባቢው ተወላጆች በአካባቢው ሰፍረው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች አስተዳደራዊ ጥያቄን ባነሱ ነዋሪዎች ላይ የተለያዩ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸማቸውን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።

ቁጥሩ ሊታወቅ ያልቻለ ሰው መሞቱን የሚናገሩት ከቀያቸው ተፈናቅለው ያሉት እማኞች አስተዳደራዊ ጥያቄን አቅርባችኋል የተባሉ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውንም ገልጸዋል።

በኮንሶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ውስጥ ወደ170 ሰዎች ለእስር ተደርገው ድብደባና ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝም እነዚሁ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

የኮንሶ ወረዳ ወደዞን አስተዳደር እንዲቀየር የቀረበን ጥያቄ ተከትሎ በአካባቢው ለቀናት የቆየ ግጭት መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።

በዚሁ ግጭት ቁጥሩ በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪ መገደሉንም ነዋሪዎችና የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

በቅርቡ በአርባ-ምንጭ ዙሪያ የተቀሰቀሰው የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት (አተት) ከኮንሶ ተፈናቅለው ለሚገኙ ነዋሪዎች ከፍተኛ የጤና ችግር መሆኑንም ለደህንነታቸው ሲሉ ተደብቀው እንደሚገኙ የተናገሩት ነዋሪዎች ለኢሳት አስታውቀዋል።

በቅርቡ ለፓርላማ ሪፖርትን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የኮንሶ ጥያቄ ሃጋዊ ምላሽን አግኝቷል ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይሁንና ህጉ የሚፈቅድልን መብት ተጠቅመን አስተዳደራዊ ጥያቄን አቅርበና የሚሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄያቸው የሃይል እርምጃን እንዳስከተለባቸው ከኢሳት ጋር በደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካልም ለችግሩ እልባትን እንዲሰጥ እነዚሁ ለደህንነታቸው ሲሉ ተደብቀው የሚገኙ ነዋሪዎች አክለው ጠይቀዋል።