ኀዳር ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ካቢኔ የከተማዋ ነዋሪዎች ጭማሪው እንዲከፍሉ የወሰነው ለከተማው ውሃ ለመዘርጋት ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣቱን በመግለጽ ነው። የክልሉ የውሃ ሀብት ም/ል ሃላፊ ለክልሉ ካቢኔ እንደገለጹት ለከተማዋ የውሃ መስመር ዝርግታ 6 ሚሊዮን 300 መቶ ሺ ብር ለማስፋፊያ ስራ ደግሞ 60 ሚሊዮን ብር በመውጣቱ፣ አጠቃላይ ወጪውን ለማስመለስ ተጠቃሚው ህብረተሰብና የንግድ ተቋማት ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ውሳኔ ተላልፏል።
በቦኖ የሚቀዱ አነስተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ከጭማሪው ነጻ ይሁኑ የሚል አስተያየት ቢቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። በዚህም መሰረት ቀድሞ በጀሪካን ወይም በእንስራ 1 ብር ከ50 ሳንቲም ይከፈልበት የነበረው ውሃ በአዲሱ ጭማሪ 2 ብር ከ30 ሳንቲም ይከፈልበታል።
በክልሉ ከፍተኛ የውሃ ታሪፍ የሚከፍሉት ባህርዳር፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ናቸው። ህዝቡ ከፍተኛ የውሃ ታሪክ እየከፈለን ነው በማለት ምሬቱን ቢገልጽም፣ በክልሉ መሪዎች ተቀባይነት አለማግኘቱን የክልሉ ወኪላችን ገልጻለች።
በሌላ ዜና ደግሞ በክልሉ የሚጣለው ግብር ገቢያችንን ያገናዘበ አይደለም በማለት በርካታ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል። ነጋዴዎቹ ፍትሃዊ የግብር አጣጣል አልተፈጸመልንም በሚል በየአካባቢው በተደረጉ ስብሰባዎች ቢያሳስቡም ምንም ምላሽ አላገኙም። ከዕቅድ በላይ ለመፈጸም ሲባል የሚጣልባቸው ከአቅም በላይ የሆነ ግብር አግባብ እንዳልሆነ ነጋዴዎች ገልጸው፤ፍትሃዊነቱን የጠበቀ የግብር አጣጣል ሳይኖር ተጨማሪ ጫና ሊደረግብን አይገባም ብለዋል