ጥቅምት ፳፫ (ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በኮማንድ ፖስት ስር እንደተደራጁ የሚገልጹ ወታደሮችና ሲቪል የለበሱ ሰዎች መንገድ ላይ ሴቶችና ወንዶች እያስቆሙ በመፈተሽ እንዲሁም ባለሃብቶችን በማስፈራራት ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን በረካታ መረጃዎች አመልክተዋል።
አሌልቱ አካባቢ አንዲት ሴት ፣ የኮማንድ ፖስት አባላት ነን ያሉ መለዮ የለበሱ ፖሊሶች ቦርሳዋን ቀምተው መውሰዳቸውን ገልጻለች። ምእራብ ጎጃም ውስጥ የሚኖሩና አድራሻቸው እንዳይታወቅ የፈለጉ ሰውም እንዲሁ ለወጣቶች ገንዘብ እየሰጡ በማደራጀት መንግስትን ለመጣል በማሴር ላይ መሆኑን ደርሰንበታል በሚል ሁለት ሲቪል የለበሱ ሰዎች መታዋቂያቸውን አሳይተው በገንዘብ የሚደራደሩ ከሆነ በነጻ እንደሚለቁዋቸው ገልጸዋል። ባለሃብቱ በማግስቱ ገንዘብ እንደሚሰጡዋቸው እንደቀጠሩዋቸውና ሁኔታውን ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል። ሰዎቹም ተመልሰው እንዳልመጡ ተናግረዋል።
የሞባይ ስልኮቻቸውን የተቀሙ በርካታ ወጣቶች፣ ለፖሊስ ቢያመለክቱም መልስ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።