ኢሳት (ኅዳር 12 ፥ 2009)
ነዋሪነታቸው በዚሁ በአሜሪካ የኦሃዮ ግዛት ኮሎምበስ ከተማ የሆነ ኢትዮጵያውያን ገቢው ኢሳትን ለመደገፍ የሚውል ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ዕሁድ አካሄዱ።
የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በተካሄደው በዚሁ ዝግጅት በኮሎምበስ ከተማና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኢሳትን በተለያየ ጊዜ ለመደገፍ ፍላጎትን ማሳየታቸውን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለዜና ዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል።
በዕለቱ ኢሳትን ለመደገፍ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ከ27ሺ ዶላር በላይ ገቢ መሰባሰቡን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በኮሎምበስ ከተማ የሚገኘው የኢሳት ድጋፍ ሰጪ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዳንዔል አበበና የፕሮግራሙ መሪ ወጣት ረድዔት ፈለቀ የኢሳትን አገልግሎት እንዲሁም ድጋፎችን ሊጠናከሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለታዳሚዎች ገለጻን ያቀረቡ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ኢሳትን በመወከል በዝግጅቱ ተገኝታለች።
የኢትዮጵያ ወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ግጥሞች በገጣሚ ፍቅርተ ጸጋዬ ከመቅረቡ በተጨማሪ ኮሜዲያን ክበበው ገዳ በዝግጅቱ በመገኘት ለታዳሚዎች ስራዎቹን አቅርቧል።
በዚሁ ልዩ የገቢ ማሰባሰብያ ዝግጅት ላይ የታደሙ ኢትዮጵያውያን የጨረታ ስነ-ስርዓት በማካሄድ ኢሳትን ለመደገፍ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አዘጋጆች አዘጋጆቹ ለኢሳት አስረድተዋል።
የኢሳትን ስድስተኛ አመት አስመልክቶ በዚሁ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ሲካሄድ የቆየው ዝግጅት በቀጣይም በአውሮፓና በተለያዩ ሃገራት እንደሚቀጥል የኢሳት አለም አቀፍ የገቢ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።