(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 11/2010) በኬንያ 8 የሃገሪቱ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣናት አልሻባብ ጥቃት መገደላቸው ተሰማ።
ባለስልጣናቱ የተገደሉት በሃገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ይጓዙበት የነበረው ተሽከርካሪ ላይ የተጠመደው ቦምብ በመፈንዳቱ ነው።
ጥቃቱን የፈጸመው በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የአልሻባብ ቡድን በተደጋጋሚ ኬንያ ወደ ሶማሊያ የላከችውን የሰላም አስከባሪ ሃይል እንድታስወጣ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል።
ይህን ተከትሎም ተከታታይ ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱንም ዘገባው አመልክቷል።
የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ቻርለስ ኦዊኖ የፖሊስ ሃይሉ አባላት ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የሃገራቸውን ዳር ድንበርና ሰላም እያስከበሩ ባሉበት ሰአት ነው ብለዋል።
የአሸባሪ ቡድኑ አልሻባብ ቃል አቀባይ በበኩሉ በጥቃቱ 10 የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ነው የገደልኩት ሲል የሃገሪቱ መንግስት ይፋ ያደረገውን አሃዝ አስተባብሏል።
በቅርቡም በዚሁ አካባቢ በተመሳሳይ አምስት የፖሊስ አዛዦች በአሸባሪ ቡድኑ መገደላቸውን ሮይተርስ በዘገባው አስታውሷል።