ኢሳት (ታህሳስ 13 ፥ 2009)
የኬንያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር በምርጫ ህግ ማሻሻያ ላይ ያደረጉት ውይይት መግባባት አለማምጣቱን ተከትሎ በሃገሪቱ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ።
ኬንያ በቀጣዩ አመት ፕሬዚደንታዊ ምርጫን የምታካሄድ ሲሆን፣ በተለይ በድምፅ ቆጠራ ሂደት ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲደረገ መንግስትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር ሲያካሄዱ መሰንበታቸው ታውቋል።
ይሁንና በሁለቱ የፓርላማ አባላት ዘንድ መግባባት ባልተደረሰበት ሁኔታ ገዥው የኬንያ ፓርቲ በፓርላማ ያለውን አብዛኛውን የመቀመጫ ወንበር በመጠቀም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀባይነት ያላገኘ ማሻሻያን ተግባራዊ እንዳደረገ ቢቢሲ ዘግቧል።
ይኸው ተግባራዊ የተደረገው አዲስ ህግ በኮምፒውተር አማካኝነት የሚሰጥ ድምፅ የቴክኒክ ችግር ባጋጠመ ጊዜ የድምፅ አሰጣጡ በወረቀት እንዲካሄድ ደንግጓል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው የወረቀት ድምፅ አሰጣጡ በስራ ላይ እንዲውል የተደረገው በድምፅ አቆጣጠር ሂደቱ ላይ ማጭበርበርን ለመፈጸም ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
“ከ800 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በኮምፒውተር አሰራር መራጮችን የመዘገበችው ህንድ የድምፅ አሰጣቱም በዚሁ መንገድ እንዲካሄድ አድርጋ ምንም ያጋጠማት ችግር የለም እኛስ ይሄንን አሰራር ለምን ተግባራዊ ማድረግ ያቅተናል?” ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥያቄ አቅርበዋል።
አዲሱ ህግ ለውይይት ለፓርላማ በቀረበ ጊዜ ተቃዋሞ እና በገዢው የኬንያ መንግስት ፓርቲ የፓርላማ አባላት ዘንድ አለመግባባትን ቀስቅሶ በፓርላማ ድብድብ መካሄዱንም የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በፓርላማ አባላቱ ዘንድ የተፈጠረውን ድብድብ ተከትሎም የቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት እንዲቋረጥ ተደርጎ በቦታው የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ከፓርላማው ቅጥር ግቢ እንዲወጡ ተደርጓል።
የአይን እማኞች በበኩላቸው በድብደባው ሳቢያ ፊታቸው በደም የተለወሰ የፓርላማ አባላት እንደነበሩ ለመገኛኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል መግባባት ሳይደረስበት የጸደቀውን አዋጅ በመቃወምም የኬንያ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በቀጣዩ ሳምንት ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ ጥሪን እንዳቀረቡ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ሃሙስ ዘግቧል።
የቀድሞ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊካሄድ ካልተቻለ በሃገሪቱ ምርጫ ብሎ ነገር አይታሰብም ሲሉ ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በኬንያ ከዘጠኝ አመት በፊት የተካሄደ ብሄራዊ ምርጫ ተቃውሞን አስነስቶ ከ1ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።