(ኢሳት ዜና–መስከረም 18/2010)በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ መንግስት የደህንነት ሰራተኞች ተጽእኖ ስር መውደቃቸውንና ለአደጋ መጋለጣቸውን ቢቢሲ ዘገበ።
በናይሮቢ የኢትዮጵያ አምባሳደር ድርጊቱ አይፈጸምም ሲሉ ማስተባበያ ሰጥተዋል።
ሒዩማን ራይትስ ዎች የተባለው አለም አቀፍ የመብት ተሟጋች የድርጊቱን አሳሳቢነት በተመለከተ በሳምንቱ መጀመሪያ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
የብሪታኒያው የዜና ማሰራጫ ቢቢሲ የአለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎችን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ባቀረበው ዘገባ የኢትዮጵያ መንግስት በኬንያና መሰል ሀገራት ውስጥ በሚፈጽመው ህገ ወጥ ድርጊት በደርዘን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተይዘው ወደ ሀገራቸው ተወስደው ለአደጋ ተጋልጠዋል።
ለቢቢሲ ቴሌቪዥን የናይሮቢ ዘጋቢ ኢማኑኤል ኢንጉዛ ለደህንነቱ ሲል ስሙን የለወጠውንና ደረጄ በሚል ስያሜ መጠራት የመረጠውን ኢትዮጵያዊ ሲያነጋግርም በናይሮቢ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ነግሮታል።
የሚኖሩበት ግቢ በተደጋጋሚ መደፈሩንና የኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች በተደጋጋሚ አፍነው ሊወስዱት እንደሞከሩ ገልጿል ።
ይህም በፖለቲካ አመለካከቱ ሳቢያ በለውጥ አቀንቃኝነቱ የሚከፍለው ዋጋ እንደሆነ አስረድቷል።
የኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ኬንያ ውስጥ አምስት ጊዜ ሊያፍኑህ ሞክረዋል አሁንስ ደህንነት ይሰማሃልን? በሚል ጋዜጠኛው ላቀረበለትም ጥያቄ ደህንነት እንደማይሰማውና የኬንያ መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ጥሪውን አቅርቧል።
በናይሮቢ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኬንያ የምንወስድበት ወደ ኬንያም የምናመጣበት ምክንያት የለም።እየተባለ ያለውም ነገር ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ ሪፖርቱን አስተባብለዋል።
ነገር ግን በሀገሪቱ የጸጥታ መስሪያ ቤት ስለሚፈጸመው ድርጊት የአምባሳደሩ እውቀት እስከምን ድረስ እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።
ምክንያቱም የሀገሪቱ የደህንነት መዋቅር ከመንግስታዊ ቅርጽ ይልቅ ድርጅታዊ መዋቅር እንዳለው በተቋሙ የሰሩ ባለሙያዎች ማጋለጣቸው ይታወሳልና ነው።
ቢቢሲ በዚህ ዘገባው የኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ድንበር እየተሻገሩ በሚፈጽሙት ድርጊት ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያንንም አስታውሷል።
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ተላልፎ ተሰቷል ያለው የቢቢሲው ዘጋቢ ኢማኑኤል ኢንጉዛ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለ አዲሱ ሪፖርት የሰጡትን ማስተባበያም አካቷል።