ኢሳት (የካቲት 8 ፥ 2009)
የኬንያ ፍርድ ቤት ለሁለት ወር የቆየውን የሃኪሞች የስራ ማቆም አድማ እንዲያበቃ አላደረጉም ባላቸው ሰባት የሃኪሞች ማህበር አባላት ላይ ያስተላለፈውን የእስር ቅጣት በመቃወም በግል ተቋማት የሚሰሩ ሃኪሞች ተቃውሞን ተቀላቀሉ።
መንግስት ከአራት አመት በፊት የገባውን የደሞዝ ጭማሪ ተግባራዊ አላደረገም ያሉ ወደ 5ሺ አካባቢ የሚጠጉ የሃገሪቱ የህክምና ባለሙያዎች ተቃውሞአቸውን ለሁለተኛ ወር መቀጠላቸውን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል።
ይሁንና የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሃኪሞቹ ሰባት የማህበር አባላት በመንግስትና በህግ አካላት የቀረበን ጥያቄ በማክበር ተቃውሞን አላስቆሙም በሚል ሰኞ ለአንድ ወር እስራት እንዲቀጡ ውሳኔን መስጠቱ ታውቋል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ባስተለለፉ በጥቂት ሰዓታት በተለያዩ የግል የህክምና መስጫ ተቋማት የሚሰሩ ሃኪሞች ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ማክሰኞች የስራ ማቆም አድማውን ተቀላቅለዋል።
ለሁለት ቀን የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ የጀመሩት እነዚሁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሃኪሞች የወሰዱት እርምጃ የእስር ቅጣት ለተላለፈባቸውና መብታቸውን በመጠየቅ ላይ ላሉ ሃኪሞች አጋርነታቸውን ለማሳየት እንደሆነ አስታውቀዋል።
በተቃውሞው ወቅት ለእስር የተዳረጉት ሰባት ሃኪሞች የማይለቀቁ ከሆነም፣ ሃኪሞቹ ቀጣይ እርምጃን እንደሚወስዱ ያሳሰቡ ሲሆን፣ የኬንያ የህክምና ባለሙያዎች ተቃውሞ በሃገሪቱ የጤና አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል።
ለሁለተኛ ወር የስራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙ 5ሺ አካባቢ የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ሰባቱ አባላት ካልተለቀቁ ከሃገሪቱ መንግስት ጋር ምንም አይነት ድርድርና ግንኙነት እንደማያደርጉ አስታውቀዋል።
በድርጊቱ የተቆጡ ዶክተሮች በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተቃውሞን ለማሰማት አደባባይ ቢወጡም የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞን በሃይል ለመበተን ሙከራ ማድረጋቸውን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
የሃኪሞቹ የማህበር አባል ተወካይ የሆኑት ቱራኒራ ካኡጊርያ መንግስት መብታቸውን ለመጠየቅ በተነሱ ባለሙያዎች ላይ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ተቃውሞን ዕልባት ከመስጠት ይልቅ ሊያባብሰው እንደሚችል አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት አንድ የኬንያ ዶክተር በወር ከ400 እስከ 800 የአሜሪካ ዶላር የሚከፈለው ሲሆን፣ የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት ደግሞ ወርሃዊ ደሞዛቸው 14ሺ ዶላር መሆኑን ጋዜጣው አስነብቧል።
በቅርቡ ተቃውሞ እንዲያበቃ ጥያቄን ያቀረቡት የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በተቃውሞ ሳቢያ ወደ 20 የሚጠጉ ታማሚዎች መሞታቸውን ገልጸው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
የሃገሪቱ መንግስት ዶክተሮቹ የ180 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ያቀረቡት ጥያቄን ለማሟላት እንደማይችል በመግለጽ ግማሽ ያህሉን ግን ለመጨመር ፍላጎትን አሳይቷል። ይሁንና ሃኪሞቹ ያቀረቡት ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ምላሽን ካላገኘ ተቃውሞአቸው ቀጣይ እንደሚሆን አስታውቀዋል።