በኬንያ ከተዘጉት ሶስት የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሁለቱ ስራ ጀመሩ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2010)

የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት ሰይመው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ የሚያሳየውን ትዕይንት ለመዘገብ በመንቀሳቀሳቸው ከተዘጉት ሶስት የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሁለቱ ስራ መጀመራቸው ታወቀ።

ሲትዝን የተባለው የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ግን አሁንም ከሳምንት በላይ ስርጭቱ እንደተቋረጠ ይገኛል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 30/2018 የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና እጩ ፕሬዝዳንት የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት ሰይመው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ የሚያሳየውን ትዕይንት በማሳየታቸው የተዘጉት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስርጭታቸውን እንዲቀጥሉ በፍርድ ቤት ቢወሰንም የኬንያ ባለስልጣናት ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው በማለት ተከራክረዋል።

የኬንያ አክቲቪስቶች ባደረጉት ያልተቋረጠ ጥረትና ድርጊቱ የሀገሪቱን ሕገ መንግስት የሚጻረር ነው በማለት ባቀረቡት አቤቱታ ከተዘጉት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሁለቱ ትላንት ስርጭታቸውን ጀምረዋል።

ሲትዝን በተባለው የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የተጣለው እገዳ ግን አሁንም ሳይነሳ ቀጥሏል።

ኬ ቲ ኤንና ኬ ቲቪ የተባሉት የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለአንድ ሳምንት ያህል ከተዘጉ በኋላ ወደ አየር መመለሳቸውን በኬንያ የሚታተሙ ጋዜጦች በዘገባቸው ላይ አስፍረዋል።