ኀዳር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኬንያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም በማለት የኬንያ ስደተኞች ቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ ማሰር መጀመራቸውንና እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው 54 የሚሆኑ ስደተኞች መታሰራቸውን የአገሪቱ ፓሊስ አስታውቋል።
ኬንያን ለመሸጋገሪያነት በመጠቀም በታንዛኒያ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ የሚሞክሩ ሕገወጥ ስደተኞች ናቸው በማለት የጸጥታ ኃይሎች መግለጫ ቢሰጡም ከሌሎች ዜጎች በተለየ ኢትዮጵያዊያን ላይ ያነጣጠረው እስርና እንግልት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ከኬኒያ ጋር ባደረገው ስምምነት ምክንያት በኬንያ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ ድንበር በመሻገር በሕገወጥ መንገድ አፍኖ መውሰድ፣መግደልና አድራሻቸውን ማጥፋት ሳያንሰው ከኬኒያ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያዊያን ላይ ገዥው መንግስት የሚፈጽመው በደል መሆኑ እየተገለጸ ነው። ፓሊስ ከ20 በላይ ወደ ታንዛኒያ የሚወስዱ መተላለፊያ መንገዶችን ዘግቶ ፍተሻውን አጠናክሮ መቀጠሉንም ካፒታል ኒውስ አክሎ ዘግቧል።
በተጨማሪም ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሞከሩ 66 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በማላዊ ተራራዎች ከተደበቁበት ስፍራ መያዛቸውንና በሕገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ በመግባታቸው ለፍርድ እንደሚቀርቡ የድንበር ፖሊስ አዛዡን ኢንስፔክተር ሞዮን ጠቅሶ ናያሳ ታይም ዘግቧል።