በኬንያ በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በኢህአዴግ የደህንነት ሃይሎች ወከባ እየደረሰባቸው ነው

ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2008)

ከኢህአዴግ መንግስት ሸሽተው በኬንያ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግስት ባሰማራቸው የደህንነት ሰዎች እንደሚዋከቡ ተገለጸ።

በኬንያ የሚታተመው ኦኬ አፍሪካ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በኬንያ የሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውና ንብረታቸውን በኢህአዴግ የደህንነት ሃይሎች ከመዘረፋቸው በላይ፣ የማስፈራራት ድርጊትም ይፈጸምባቸዋል በማለት አትቷል።

ታሪኩ ደበላ የሚባል አንድ በኬንያ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛን ዋቢ አድርጎ የዘገበው ጋዜጣው፣ በናይሮቢ ከተማ ኢስትሌይ በሚባል አካባቢ አራት የኢህአዴግ የደህንነት ሃይሎች ከመኪና በመውረድ 200 ዶላርና ሞባይል ቀፎ አስገድደው ከወሰዱበት በኋላ፣ በአማርኛ ወይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አብረህ ስራ፣ አለዚያ ሞት ይጠብቅሃል ብለው እንደዛቱበት መናገሩን ጋዜጣው ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ መንግስት እስር፣ ግርፋትና ወከባ ለማምለጥ ወደኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ያሰቡትን ከለላ ከኬንያ መንግስት እንዳማያገኙና ለስደተኞች መደረግ የነበረበት ጥበቃ እንደማይደረግላቸው ጋዜጣው አስነብቧል። የኢትዮጵያ መንግስት ረጅም እጆች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኬንያ ውስጥም አሉ በማለት ወደኬንያ መሰደድ ከኢትዮጵያ መንግስት መንጋጋ እንደማያድናቸው ጋዜጣው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።

ጋዜጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ዋቢ በማድረግ ባለፈው ጥር 2016 የፈረንጆች ወር ብቻ የኬንያ የጸጥታ ሃይሎች 25 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ለኢትዮጵያ ለደህንነት ሃይላት አሳልፈው መስጠታቸውን ገልጿል።

እነዚህ ስደተኞች ወደሃገራቸው በግዳጅ ስለመመለሳቸው በኬንያ የሚኖሩ የኦሮሞ ኮሚኒቲ መሪዎች አረጋግጠዋል ሲል ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል። ሌሎች ስደተኞቹም ለኢትዮጵያ መንግስት በሚሰሩ በኬንያ የድንበር ጠባቂዎችና አስገድዶ የመመለስ ሃላፌዎች (Deportation Officers) ስለላ እንደሚካሄድባቸው፣ ወከባና ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው የጥቃቱ ሰለባዎችን ዋቢ በማድረግ ጋዜጣው አስነብቧል።

በናይሮቢ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የስደተኞች ኦፊሰር  ለኦኬ አፍሪካ እንደተናገሩት፣ ኬንያን የመሳሰሉት አገራት ትክክለኛው የስደተኛች ፖሊሲ አይከተሉም። ስደተኞችን ህግና ስርዓት በተከተለ መልኩ ከማስተናገድ ይልቅ የኢትዮጵያን የእድገትና የስኬት ዜና ብቻ ነው መስማት የሚፈልጉት ሲሉ ለዚሁ ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአለም አቀፍ የስደተኛ ድርጅቶች ኢትዮጵያ የምትፈጽመውን የሰብዓዊ ጥሰት የማይናገሩበት ምክንያት ከሱዳን፣ ኤርትራና ሶማሌ ሸሽተው በኢትዮጵያ የሚኖሩ 700,000 የሚጠጉ ስደተኞች ዕጣ ፋንታ እንዳይወሳሰብ ከመፈለግ አንጻር ሊሆን እደሚችልም ጋዜጣው ዘግቧል።

እኤአ በ2015 በኬንያ 160,427 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስደተኞች እንደነበሩ የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅትን ዋቢ አድሮ ኦኬ አፍሪካ ዘግቧል።