(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 15/2010) በኬንያ ሀሙስ ለማካሄድ የታቀደው ምርጫ በእቅዱ መሰረት የሚካሄድ መሆኑ ታወቀ።
ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው ማመልከቻ ከሰባቱ ዳኞች ሁለቱ ብቻ በመገኘታቸው ሳይታይ መቅረቱ ታውቋል።
ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ምርጫውን ለማደናቀፍ ጠርተውት የነበረውን የሰላማዊ ሰልፍ እቅድ በመሰረዝ ደጋፊዎቻቸው ቤት በመዋል ቀኑን እንዲያሳልፉ መክረዋል።
በኬንያ ሀሙስ በድጋሚ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተወሰነለት የጊዜ ገደብ መሰረት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።
ምርጫው ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ በሚል በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው ማመልከቻ ከሰባቱ ዳኞች ሁለቱ ብቻ ናቸው የተገኙት በሚል ሳይታይ ቀርቷል።
ዳኞቹ ፍርድ ቤት ላለመምጣት የተለያየ ምክንያት አቅርበዋል።
አንደኛው በህመም ምክንያት ሳይገኙ ሲቀሩ ሌሎቹ ደግሞ ከከተማ ውጪ በመሆናቸውና በረራ ባለማግኘታቸው እንዲሁም መናገር በማይፈልጉት ምክንያት ቀርተናል ብለዋል።
ፍሎሜና ሞዊሉ የተባሉት ዳኛ ሹፌር ትላንት በጥይት ተመቶ በመቁሰሉ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
ዳኛዋ በዛሬው ችሎት ካልተገኙት አንዷ ናቸው።
ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ አይሆንም ሲሉ የአለምአቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን የመታዘብ ተሳትፏቸውን ቀንሰዋል።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ምርጫው በታቀደለት መሰረት ሀሙስ እንደሚካሄድ ሲያስታውቁ የተቃዋሚ መሪው ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው እንደማይሳተፉ በድጋሚ ገልጸዋል።
ለደጋፊዎቻቸውም በምርጫው እንዳይሳተፉ ጥሪ አድርገዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ሃላፊ ዋፉላ ቼቡካቲ እንደገለጹት ከጸጥታና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት በደረሳቸው ማረጋገጫ መሰረት ሀሙስ ከጠዋቱ 12 ሰአት የምርጫ ጣቢያዎች ክፍት ይሆናሉ ብለዋል።
በምርጫ ጣቢያዎች ለሚሰሩ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ደህንነት ግን ዋስትና አንሰጥም ብለዋል።
ኦዲንጋ ናይሮቢ ላይ ባደረጉት ንግግር ከአሁን በኋላ ናሽናል ሱፐር አሊያንስ በመባል የሚታወቀውን ፓርቲያቸውን ወደ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መቀየራቸውን አስታውቀዋል።
የጠሩትን ሰላማዊ ሰልፍ በመሰረዝም ደጋፊዎቻቸው ሀሙስ በቤታቸው በመዋል እንዲያሳልፉ መክረዋል።
ምክንያቱም አሉ ኦዲንጋ ደም የጠማው መንግስት በመሆኑ ይጨርሳችኋል ብለዋል።
ባለፈው ነሀሴ የተደረገውና ተቀማጩ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበትን ምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል በሚል የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰረዘው በኋላ በተፈጠረው ብጥብጥ የ67 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።
የሀሙሱ ድጋሚ ምርጫም ደም መፋሰስ እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።
ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሚፈጠር ብጥብጥ በተለይ ከ2007 ጀምሮ እስካሁን ወደ 1600 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።