መስከረም ፯(ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከስድስት አመታት በፊት በኬንያ ከተደረገው ምርጫ ጋር በተያያዘ ለተገደሉት ሰዎች ተጠያቂ የተደረጉት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ዘ ሄግ በሚገኘው አለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት በአካል ቀርበው የመጀመሪያዋን የጉዳቱ ሰለባን ቃል አዳምጠዋል።
ማንነቷ በውል ያላታወቀችው መስካሪ በረብሻው ጊዜ የደረሰውን ግፍ በዝርዝር አስረድታለች፡፤ ም/ል ፕሬዚዳንቱ ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ታውቋል። ሌሎች 22 ምስክሮችም በተከታታይ ቀርበው እንደሚመሰክሩ ታውቋል።
የአገሪቱ መሪ ኡሁሩ ኬንያታም እንዲሁ ለጠፋው የሰው ህይወት ተጠያቂ በመሆን ከ2 ወር በሁዋላ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ኬንያ ከአለማቀፉ ፍርድ ቤት አባልነት እንድትወጣ በፓርላማ ድምጽ እንዲሰጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ ህብረት ለአለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እውቅና እንዳይሰጥ መጠየቃቸው ይታወቃል።
የሱዳኑ መሪ ጄኔራል አልበሽርም እንዲሁ በአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ተከሰው የእስር ማደኛ እንደወጣባቸው ይታወቃል።