(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2010)
ሕንድና ፓኪስታን በሚወዛገቡባት የካሽሚር ግዛት አዲስ ውጥረት ነገሰ።
የህንድ ወታደሮችን ጨምሮ በትንሹ 5 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ መካሄዱም ታውቋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 የተካሄደውን የተኩስ ማቆም ስምምነትን ተከትሎ ጃሙና ካሽሚር በተባለ ስፍራ ላይ እንዲወሰኑ የተደረገውን ወታደራዊ የድንበር መስመር የተቀበሉ ቢሆንም በቀደሙት አመታት ህንድ ፓኪስታንን ስትወነጅል ቆይታለች።
ሆኖም ከ15 አመታት ወዲህ የአሁኑ ከፍተኛና የሁለቱን ሀገራት ወታደሮች ለተኩስ ልውውጥ የጋበዘ እንደሆነም አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።
ዛሬ ማለዳ ላይ የ52 አመት ሴትን ጨምሮ የሁለት ሲቪሎች እንዲሁም አንድ ህንዳዊ የድንበር ጠባቂ ወታደር መገደል የቀሰቀሰው ውጥረት የሁለቱን ሀገራት ወታደሮች ለተኩስ ልውውጥ የጋበዘ ሆኗል።
ሲቪሎቹና የድንበር ጠባቂው የተገደሉት ከፓኪስታን ወገን በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ እንደሆነም ታውቋል።
አርብ ማለዳ ከደረሰው ጥቃት ቀደም ብሎ ሀሙስ ዕለትም አንዲት የ17 አመት ወጣት እንደተገደለች የገለጹት የህንድ የአካባቢው ባለስልጣናት 24 ሰአታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 5 ያህል ሰዎች መገደላቸውንና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
ፓኪስታን ስምምነቱን በመጣስ ወታደሮቿ በህንድ ይዞታ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ አድርጋለች በማለት ህንድ በተደጋጋሚ ክስ ስታቀርብ መቆየቷም ታውቋል።
ከፓኪስታን ወገንም ዛሬ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በህንድ ግዛት ውስጥ እንደተፈጸመም አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል።
ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ እየጠነከረ የመጣውና አሁን የተባባሰው ሁኔታ በቀደሙትም ተከታታይ አመታት መጠነኛ ግጭቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
ፓኪስታን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1947 ከሕንድ ተገንጥላ የራሷን ነጻነት ካገኘች ወዲህ በካሽሚር ግዛት ሳቢያ በሁለቱ መንግስታት መካከል ሁለት ጊዜ ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዷል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1989 ለካሽሚር ነጻነት የሚታገሉ አማጽያን ከህንድ ጋር ባደረጉት ውጊያ ከ70 ሺ በላይ ሰዎች አልቀዋል።
በአካባቢው በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊየን የህንድ ወታደሮች መስፈራቸውም ይታወቃል።
በካሽሚር ሳቢያ የሚወዛገቡት ህንድና ፓኪስታን ሁለቱም የኒዩክለር መሳሪያ የታጠቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።