በካሳንቺስ የሚኖሩ በ 10 ሺዎች የምቆጠሩ ነዋሪዎች ለልማት በሚል ሰበብ ከመኖሪያ ቦታቸው ሊነሱ ነው

ኢሳት (ነሃሴ 4, 2008)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከካዛንቺስ ቤተመንግስት ዙሪያ በተለምዶ ግቢ ገብርዔል ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ እስከ ኡራዔል ቤተክርስቲያን ድረስ ያሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ለልማት በሚል ሰበብ ለማስነሳት የተያዘው እቅድ በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ከከተማው አስተዳደር ከነዋሪዎች የተላለፈን መልዕክት ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ተቃውሞን እያቀረቡ እንደሆነ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል። kazanchis

ለበርካታ አመታት በአካባቢው እንደኖሩ የተናገሩት ነዋሪዎች የከተማዋ አስተዳደር ከሰጠው ማሳሰቢያ ውጭ እስካሁን ድረስ በካሳ ክፍያና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አለመካሄዱን አስታውቀዋል።

በነዋሪዎች ይዞታ ላይ ቅድሚያ ጨረታ ተካሄዷል በማለት ጉዳዩን ያስረዱት ምንጮች ከመኖሪያ እና ከንግድ ድርጅቶቻቸው እንዲነሱ የተጠየቁት ነዋሪዎች ቅሬታቸውንና ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሚመለከተው አካል በመግለጽ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።

የከተማዋ አስተዳደር በቅርቡ በቦሌ እና ላፍቶ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችን ለልማት በሚል ለማስነሳት የወሰድው እርምጃ ተቃውሞን ቀስቅሶ ሁለት የጸጥታ አባላትን ጨምሮ አንድ የወረዳ ስራ አስፈጻሚ መገድላቸው ይታወሳል።

በነዋሪዎች የተነሳን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ከ20 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ባለፈው ወር በጉዳዩ ዙሪያ አስቸኳይ ምክክክርን ያካሄደው የከተማዋ አስተዳደር ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ አካባቢዎችን የማፍረሱ ሂደት እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል።

ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚኖሩበት የሚነገርለትን እና ከግቢ ገብርዔል እስከ ኡራዔል ቤተክርስቲያን ድረስ የሚሸፍነውን ሰፊ መንደር ለልማት በሚል ለማንሳት መወሰኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት አስረድተዋል።

ከመኖሪያና የንግድ አካባቢያቸው በመነሳታቸው በኑሮአቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚፈጠር የገለጹት ነዋሪዎቹ አስተዳደሩ የማህበረሰቡን ችግር ግምት ውስጥ ሳያስገባ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የተያዘው እቅድ በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተከትሎ አስተዳደሩ እቅዱን እንዲሰርዝ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁንና የእቅዱን ተግባራዊ አለመደረግ ምክንያት በማድረግ የከተማዋ አስተዳደር ለባለሃብቶች ሊሰጥ ያሰበውን መሬት በከተማዋ ባሉ ቦታዎች እንዲያተኩር መገደዱን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።