በካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት ገቢ ከ 100 ሺ ዶላር በላይ ድጋፍ አሰባሰቡ

ኢሳት (ጥቅምት 8 ፥ 2009)

ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት በኦክላንድና ሳንሆሴ ከተሞች የሆን ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜና እሁድ ባካሄዱት ልዩ የኢሳት ገቢ ማሰባብሰቢያ ዝግጅት ከ100 ሺ ዶላር (ከ 2 ሚሊዮን ብር) በላይ ድጋፍ አሰባሰቡ።

የሁለቱ ከተሞች የገቢ አሰባሳቢ አስተባባሪዎች ቅዳሜ በኦክላንድ እሁድ ደግሞ በሳንሆሴ ከተሞች የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታና በደማቅ ስነስርዓት መከናወኑን ለኢሳት ገልጸዋል።

በኦክላንድ ከተማ ተካሂዶ በነበረው በዚሁ ዝግጅት የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ የስደተኛው ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ ብፁዕ አቡነ መልከጻዲቅና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች በመገኘት ለታደሙ ኢትዮጵያውያን ንግግር አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ዝግጅት ዕሁድ በሳሆሴ ከተማ በተካሄደው ስነስርዓት አባ ገብረ ገብርዔል ከኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ሼኽ መሃመድ የሙስሊሙ ማህበረሰብን በመወከል በየግል መልዕክትን አስተላልፈዋል።

በዚሁ የኢሳት ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በሳን ሆሴ ከተማ በተካሄደው ዝግጅት ዶ/ር ብርሃኑ ሊንጂሶ በሚዲያ ዙሪያ ትምህርታዊ ገለጻን አቅርበዋል።

በሁለቱ ከተሞች በተካሄደው ዝግጅት የጨረታ ገቢን ጨምሮ በአጠቃልይ ከ100ሺ ዶላር (ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ) ሊገኝ መቻሉን አስተባባሪዎች አስታውቀዋል። የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል የሚያንጸባርቁ ምስሎች በስነስርዓቱ ወቅት ለገቢ ማሰባሰቢያነት ለጨረታ ቀርቦ እንደነበር ታውቋል።

ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ኢሳትን በመወከል እንዲሁም ኮሜዲያን ክበበው ገዳ በክብር እንግድነት በዝግጅቱ የታደሙ ሲሆን አርቲስት ተስፋዬ ለማ በሁለቱም ከተሞች መድረክ የማስተዋወቅ ስራ ማከናወኑን አስተባባሪዎቹ አከለው ገልጸዋል።

የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በመካሄድ ላይ ያሉ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች በቀጣይ ወራቶች በተለያዩ ስፍራዎች እንደሚካሄዱ የኢሳት አለም አቀፍ የገቢ ማስተባበሪያ ኮሚቴ አስታውቋል።